“ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተመድ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ጉባዔ ያካፈሉት ተሞክሮ ኢትዮጵያ በለውጥ ተምሳሌትነት እንድትታይ ያስቻለ ነው” ቢልለኔ ስዩም

49

ባሕር ዳር፡ ኅዳር 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የኦስትሪያ ቆይታን በማስመልከት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሀላፊ ቢልለኔ ስዩም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በኦስትሪያ ያደረጉት ቆይታ ሁለት አላማዎች እንዳሉት አንስተው ክብር እንግዳ ሆነው በመገኝት ቁልፍ መልእክት አስተላልፈዋል ብለዋል።

በዋነኝነት ደግሞ ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ያከናወነቻቸውን የለውጥ ስራዎችና ያገኘቻቸውን አመርቂ ውጤቶች በጉባኤው አካፍላለች ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ባለፉት 5 አመታት በፖሊሲ ደረጃ ከፍተኛ ለውጦችን እያመጣች መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማመልከታቸውንም ሀላፊዋ አንስተዋል።

በዚህም ተስማሚ የኢንቨስትመንት ከባቢን በመፍጠር፣ ማክሮ ኢኮኖሚውን በማስተካከልና ተጨማሪ ማሻሻያዎችን በማከናወን ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ምቹ ሁኔታዎች መቀየሷን ማመላከታቸውንም ገልጸዋል።

የሀገር በቀል የለውጥ አጀንዳ ዋና ምሰሶ በሆኑት ማኑፋክቸሪንግ፣ ግብርና፣ አይሲቲ፣ ማዕድንና ቱሪዝም በኩል የተከናወኑ ተግባራትንና ለውጦችን በጉባኤው ማካፈላቸውን አብራርተዋል።

የኢንዱስትሪ ዘርፉን በተመለከተ በአርንጓዴ ስልትና ፖሊሲ በታዳሽ ሃይል ልማት ላይ አተኩራ እየሰራች መሆኑን ማስገንዘባቸውንም አንስተዋል።

በስራ ፈጠራ ረገድ ዜጎች በሀገራቸው ልማት እንዲሳተፉና የግሉ ዘርፍ ተዋንያን የኢኮኖሚ ተሳትፎ እንዲጠናከር እየተከናወኑ የሚገኙ ተጨባጭ ስራዎችን ማካፈላቸውንም ሃላፊዋ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ጀነራል ገርድ ሙለር ኢትዮጵያ ባለፉት 5 አመታት ያከናወነቻቸውን የለውጥ ስራዎች እንደ ተምሳሌትነት መጥቀሳቸውን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሶስት እጥፍ የምርት እድገት ማሳየቷንና ይህም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ተጨባጭ እርምጃ እንደሆነ መመስከራቸውን ገልጸዋል።

በኢንዱሰትሪው ዘርፍ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግና ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት የሚያስችሉ ተግባራት መከናወን እንደሚገባ በጉባኤው መነሳቱን ተናግረዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር የተመራ ልዑክ ጅግጅጋ ገብቷል።
Next articleፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ በፆታዊ ጥቃት ላይ በሚመክረው መድረክ ለመካፈል ደቡብ አፍሪካ ገቡ።