
ባሕር ዳር: ኅዳር 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት 26ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሔደ ነው። ምክር ቤቱ በአጀንዳነት ከያዛቸው ርእሰ ጉዳዮች መካከልም የከተማውን የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ የ2015 በጀት አፈጻጸም ሪፖርት አድምጧል።
የኢንተርፕራይዙን አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት አቶ ዘዉዱ ዘለቀ ኢንተርፕራይዙ የባሕር ዳር ከተማን የመንግሥት ሠራተኞች እና የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ለማሻሻል በደንብ ቁጥር 17/2009 ተቋቁሞ በ2012 ዓ.ም ሥራ መጀመሩን ጠቅሰዋል።
➥ በ20 አውቶቡሶች ለክልሉ፣ ለባሕር ዳር እና ለባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ የመንግሥት ሠራተኞች በድምሩ ለ9 ሺህ 10 ሠራተኞች የጧት እና የማታ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሠጠ መኾኑ
➥ መነሻ እና መዳረሻ ቦታዎችን በማስፋት ለማኅበረተሰቡ በዝቅተኛ ዋጋ የትራንስፖርት አገልግሎት እየተሠጠ መኾኑ
➥ ከብክነት የጸዳ እና የተሟላ አገልግሎት ለመሥጠት የራሱ ጋራዥ፣ የነዳጅ ማደያ፣ የመኪና ማሳደሪያ ቦታ እና ቢሮ ሊኖረው እንደሚገባ
➥ በቀጣይም የሠራተኛ ቁጥር እና የቦታ ርቀት መጨመር ስለሚኖር ሙሉ አገልግሎት ለመሥጠት ራሱን የቻለ ተቋም የሚጠይቅ መኾኑን አብራርተዋል።
አገልግሎቱ ሙሉ ኾኖ የማኅበረተሰቡን ችግር የሚፈታ የተሻለ አገልግሎት ለመፍጠር የክልሉን መንግሥት ድጋፍ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ለባሕር ዳር ከተማ የሚመጥን የትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። አገልግሎቱን ለማሻሻል እና የባሕር ዳር ከተማን የሚመጥን የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሠጥ ለማድረግም ሥራዎች ይሠራሉ ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!