ከፍተኛ የውኃ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች ተግባራዊ የሚደረግ “ግድቤን በደጄ” የተሰኘ ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ፡፡

94

አዲስ አበባ: ኅዳር 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የውኃ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች ተግባራዊ የሚደረግ “ግድቤን በደጄ” የተሰኘ ፕሮጀክት ለማስጀመር በሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር እንዲሁም በውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር መካከል የስምምነት ፊርማ ተካሂዷል።

ስምምነቱ ከፍተኛ የውኃ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች ተግባራዊ ሲደረግ የንጹህ መጠጥ ውኃ ችግርን የሚቀርፍ አዲስ አሠራር ነው ተብሏል። በነዚህ አካባቢዎች ለመጠጥ ውኃ የሚውል አዲስ እና አነስተኛ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ እንደሚደረግም ተገልጿል።

ስምምነቱን የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ እና የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ናቸው የተፈራረሙት።

ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ ተግባራዊ የሚደረገው ፕሮጀክት ለአነስተኛ እርሻ እና ለመጠጥ ውኃ የሚውል አዲስ ቴክኖሎጂ ለማቅረብ እንደሚረዳ ገልጸዋል።

የጣራ ላይ ውኃን በማሰባሰብ እና በማቆር በአማራ ክልል ማዕከላዊ ጎንደር ዞን እና በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ላይ በተግባር መጀመሩም ተገልጿል። “ግድቤን በደጄ” ፕሮጀክት ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርም ነው የተብራራው።

የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ፕሮጀክቱ ዜጎችን የንጹህ መጠጥ ውኃ ባለቤት የሚያደርግ እንደኾነ አብራርተዋል፡፡ በውኃ ዘርፍ ብቻ ሳይኾን በኢነርጂ ዘርፍም አብሮ ለመሥራት ዝግጁ ስለመኾናቸውም ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
ወጣቶችን አደራጅቶ እና አሠልጥኖ ወደ ሥራ ለማስገባት ሰፊ ዕድል እንዳለውም ነው ያብራሩት።

ፕሮጀክቱ በቅርቡ በተመረጡ 87 ቦታዎች ላይ ተግባራዊ ይደረጋልም ተብሏል።

ዘጋቢ፡- ዳንኤል መላኩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከ60ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የገጠር አካባቢዎችን የሚያስተሳስር የመንገድ ግንባታ ተከናውኗል” የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር
Next article“የካርድ ቀበኛው” ሰርጆ ራሞስ