“ከ60ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የገጠር አካባቢዎችን የሚያስተሳስር የመንገድ ግንባታ ተከናውኗል” የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር

55

አዲስ አበባ: ኅዳር 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሁሉን አቀፍ የገጠር መንገድ ተደራሽነት ፕሮግራም ባለፉት ዓመታት ከ60 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የገጠር መንገዶችን የሚያስተሳስር የመንገድ ግንባታ መከናወኑን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ገልጿል፡፡

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር እና ግብርና ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ ባለፉት ዓመታት የተተገበሩ ሁሉን አቀፍ የገጠር መንገዶች ትስስርና ተደራሽነት ፕሮግራም ሪፖርት እና አዲሱ የገጠር ትስስርና ተደራሽነት ፕሮግራም ላይ ከክልል ተወካዮች ጋር እየመከረ ነው።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2030 በአፍሪካ በንጽህና ተምሳሌት ሀገር የመኾን እቅድን እውን ለማድረግ እየሠራች መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ሚኒስትር ዴኤታው መሥሪያ ቤታቸው ለዚህ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መኾኑን ነው የገለጹት።

በሁሉን አቀፍ የገጠር መንገድ ተደራሽነት ፕሮግራም ከ60 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ክረምት ከበጋ የገጠር መንገዶችን የሚያስተሳስር የመንገድ ግንባታ ተከናውኗልም ብለዋል።

በአዲስ መልክ ወደ ትግበራ ሊገባ በታቀደው የገጠር ትስስርና ተደራሽነት ፕሮግራም ላይ ከክልልና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየመከረ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጥናቱን አጠናቅቆ ፕሮግራሙ ወደ ሥራ ሲገባ ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚደረግም አስገንዝበዋል፡፡ ፕሮግራሙ ለአራት ዓመታት ቆይታ እንደሚያደርግም ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

የፕሮግራሙ በጀትም በዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ድጋፍ፣ በፌዴራል እና በክልሎች የሚሸፈን መኾኑን ጠቁመዋል።

ፕሮግራሙ ሀገር አቀፍ እንደመኾኑ በዋናነት ውስን የኾነውን የሀገር ሀብት በአግባቡ ለመጠቀምና ወደ ወጥ አሠራር እንዲመጡ ማስቻል ዋና ዓላማው መኾኑም ተገልጿል።

በገጠር መንገዶች ትስስርና ተደራሽነት ፕሮግራም የገጠሩን የማኅበረሰብ ክፍል በመንገድ በማስተሳሰር ማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ እድገት እንዲያመጣ እንደሚያስችልም ተብራርቷል፡፡ ሥራው አርሶ አደሩ ምርቱን ወደ ገበያ ወስዶ ተደራሽ እንዲያደርግ ያስችለዋልም ተብሏል።

ከአሁን በፊት ሲተገበር በቆየው በሁሉን አቀፍ የገጠር መንገድ ትስስር ተደራሽነት ፕሮግራም በሥራ እድል፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እና የገጠር ቀበሌዎችን ክረምት ከበጋ በማገናኘት ውጤት ያላቸው ሥራዎች መሠራታቸውም ተነስቷል።
በመድረኩ የዓለም ባንክ እና የክልል ተወካዮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡- ቤተልሄም ሰለሞን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በአማራ ክልል ያለውን ችግር ለመፍታት ተግባር እና ኀላፊነትን በአግባቡ መወጣት ይገባል” አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ
Next articleከፍተኛ የውኃ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች ተግባራዊ የሚደረግ “ግድቤን በደጄ” የተሰኘ ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ፡፡