
ባሕር ዳር: ኅዳር 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች ክትትል እና ቁጥጥር ከሚያደርጉባቸው ተቋማት በጋራ እቅዳቻቸው ላይ ተወያይተዋል። በወይይቱ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ የተከበሩ ፋንቱ ተስፋዬ፣ ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤን ጨምሮ የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች እና የአሥፈጻሚ ተቋማት መሪዎች ተገኝተዋል።
የቋሚ ኮሚቴዎችን የጋራ እቅዶች ያቀረቡት የሰው ሃብት እና ቱሪዝም ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አበራሽ ታደሰ አስፈጻሚ አካላት ችግሮችን ያለ መፍታት፣ የማወሳሰብ እና ችላ የማለት ችግሮች መኖራቸውን አመላክተዋል። የአገልግሎት አሰጣጡ ሠፊ ችግር እንዳለበትም አንስተዋል። ዜጎችን በሚያንገላቱ አሥፈጻሚ አካላት ተጠያቂነት እንዲኖር እንሠራለንም ብለዋል።
የሕዝብን ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ እንደሚሠራም ገልጸዋል። አስፈፃሚ አካላት ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ ቁጥጥር እና ክትትል እንደሚያደርጉም አንስተዋል። የሥራ እድል ፈጠራ በሁሉም ተቋማት ትኩረት መሠጠቱን እንደሚከታተሉም አመላክተዋል። በመደበኛ እና መደበኛ ባልኾኑ የመስክ ምልክታዎች የመሰረተ ልማት ሥራዎችን መቆጣጠር እንደሚገባም ገልጸዋል።
ምርመራ እና ማጣራት የሚያስፈልጋቸውን የሕዝብ አቤቱታዎችን ቦታው ድረስ ሄዶ የማረጋጋጥ ሥራ ይሠራልም ተብሏል። የሚወጡ ሕጎች ከሕዝብ ወግ፣ ባሕል እና እሴት ጋር የተቆራኙ እንዲኾኑ እንደሚሠራም አመላክተዋል።
ግልጽነት፣ አሳታፊነት እና ተጠያቂነት፣ መርሕ መከበሩን የማረጋገጥ ተግባርም ትኩረት ይደረግበታል ተብሏል። የመልካም አሥተዳደር ችግሮች በምክር ቤቱ ቀርበው ውይይት እንዲደረግባቸው እና መፍትሔ እንዲሰጣቸው እንደሚሠሩም አመላክተዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ቁጥጥር እና ክትትል መደጋገፍን መርሕ ያደረገ እና ችግሮችን መፍታት በሚቻልባቸው መንገዶች እንደሚከናወንም ተገልጿል። የሚወጡ ሕጎች የሕዝብን መብት እና ጥቅም የሚያስከብሩ እንዲኾኑ ትኩረት እንደሚሰጣቸውም ተመላክቷል።
የሁሉም ክፍተት ድምር ውጤት ሕዝብን ለችግር ዳርጓል፤ በተቀናጀ ሥራ የተማረረውን ሕዝብ መካስ ይገባል ብለዋል።
በግምገማው የተገኙት የቋሚ ኮሚቴው አባላት እና አስፈጻሚዎች ወቅቱ እና አቅምን ታሳቢ ያደረጉ አቅጣጫዎችን እንዲሠጡ ጠይቀዋል። ወቅቱን ግንዛቤ ውስጥ ያላደረገ አቅጣጫ ተፈጻሚ ሳይኾን እንደሚቀርም ተናግረዋል።
የክልሉ ቀዳሚ አጀንዳ ሰላም መኾኑንም ገልጸዋል። የክልሉን ሕዝብ የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በጋራ መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል። ቋሚ ኮሚቴው አንጻራዊ ሠላም ባለባቸው አካባቢዎች ድጋፍ እና ክትትል ማድረግ እንደሚገባውም አመላክተዋል።
ሕዝቡን የሚያማርሩ ተቋማትን እንዲቆጣጠሩም ጠይቀዋል። በሪፖርት የሚቀርቡ እና የሚሠሩ ሥራዎች እንደሚለያዩም አንስተዋል። ችግሮችን ደፍረው የሚያወጡ እና ለመፍትሔያቸው የሚሠሩ ተቋማትም ሊበረታቱ ይገባል ነው ያሉት።
የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባዔ አማረ ሰጤ በሕዝቡ ዘንድ የሚነሱ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን ተናግረዋል። በአማራ ክልል ያለው የአመራር መለዋወጥ እና ተረጋግቶ አለመሥራት በአስፈጻሚ ተቋማት ላይ ችግር እንዲፈጠር አድርጎታል ነው ያሉት። ጊዜ በመሥጠት እና በመደገፍ የተሰጠውን ኀላፊነት እንዲወጣ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል። ጊዜ ተሰጥቶት በማይሠራ መሪ ላይ እርምጃ ለመውሰድም ይመቻል ነው ያሉት።
የክልሉ አስፈፃሚ አካላት ጠንከር ብለው የሕዝቡን ጥያቄዎች መፍታት ይገባቸዋል ብለዋል። የአማራ ክልል ጥያቄ ከሰላማዊ አማራጮች ውጭ መፍታት አይቻልም ብለዋል።
ለሰላም ሁሉንም ዋጋ መክፈል እንደሚገባ ነው የተናገሩት። በአማራ ክልል ያሉ የሕዝብ ጥያቄዎች እንዲፈቱ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። በጥላቻ እና በግጭት ሀገርም አትጸናም፣ የሕዝብ ጥያቄም አይመለስም ነው ያሉት። ችግሮቻችን በውይይት እና የጋራ በማድረግ መፍታት ይገባናል ብለዋል።
የሕዝብ ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም አመላክተዋል። የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ መደማመጥ ይጠበቃልም ብለዋል። በክልሉ ያለውን አንጻራዊ ሠላም ዘላቂ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ፋንቱ ተስፋዬ ምክር ቤቱ የተሰጠውን ሥልጣን እና ተግባር በአግባቡ ለመወጣት እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ክልሉ አሁን ያለበት ነባራዊ ሁኔታ ውስብስብ ነው ያሉት አፈ ጉባዔዋ ሁሉም የተሰጠውን ተግባር እና ኀላፊነት መወጣት ይገባቸዋል ነው ያሉት።
ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ምክር ቤቱ የራሱን ድርሻ መወጣት አለበትም ብለዋል። የሕዝብ የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሀብት እና የማኅበራዊ ጥያቄዎች አለመመለሳቸው ለተፈጠረው ችግር መነሻ መኾናቸውንም ገልጸዋል። ተቋማት እቅዶችን መፈጸም እንደሚገባቸውም አመላክተዋል። የሕዝብን ጥያቄ መሠረት ያደረጉ መልሶች መመለስ እንዳለባቸውም ገልጸዋል። ያልተመለሱበትን ምክንያት ማስረዳት እና መግባባት ላይ መድረስ ይገባል ነው ያሉት።
የሕዝብ ችግሮችን መፍታት አለመቻል የሕዝብ አመኔታን ያሳጣል ያሉት አፈ ጉባዔዋ የሕዝብ አመኔታ እንዲኖር ችግሮችን መፍታት ይገባል ነው ያሉት። የአገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል እንደሚገባም አሳስበዋል። በቅንጅት በመሥራት ክልሉ ካለበት ውስብስብ ችግር ማውጣት እንደሚገባም አመላክተዋል።
ሕዝቡን ከሆደ ባሻነት የማውጣት ሥራ መሥራት ግድ እንደሚልም አሳስበዋል። የሕዝብን ጥያቄ መስማት እና እንዲፈታ ማድረግ ከምክር ቤት አባላት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል። እቅዶች ላይ መግባባት በመፍጠር ለተፈጻሚነታች መሥራት ይገባልም ብለዋል።
የሚወጡ ሕጎችን እና አዋጆችን ማክበር እና መተግበር አስፈላጊ መኾኑንም ተናግረዋል። የሕዝብን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባልም ብለዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!