የሥራ አጥ ቁጥር መበራከት ለወንጀል መበራከት ምክንያት በመኾኑ አሁንም መፍትሄ እንደሚያሻው የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት አባላት ተናገሩ፡፡

42

ባሕር ዳር፡ ኅዳር 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት 4ኛ ዙር 11ኛ ዓመት 26ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው። ጉባኤው በቆይታው በሰባት አጀንዳዎች ላይ ውይይት ያደርጋል ተብሎም ነው የሚጠበቀው።

የተቋማትን የ2015 በጀት ዓመት አፈጻጸም እና የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ ገምግሞ ማጽደቅ እንዲሁም የአከራይ ተከራይ ደንብ ማውጣት ከአጀንዳዎቹ መካከል እንደኾነም ተገልጿል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የከተማ አሥተዳደሩን የ2015 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በሪፖርታቸው እንደገለጹት:-

👉 በከተማ አሥተዳደሩ 50 ሺህ 385 ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል

👉 ለ166 የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ፈላጊ ማኅበራት ቦታ ሰጥቷል

👉 በተለያዩ አማራጮች 971 ቤቶች ተገንብተው ለተጠቃሚዎች ተላልፈዋል

👉 በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ 24 ሺህ 237 የከተማው ነዋሪዎች የሴፍቲኔት ተጠቃሚ እንዲኾኑ ተደርጓል

👉 ለ1 ሺህ 05 የልማት ተነሺዎች 800 ሚሊዮን ብር ካሣ ተከፍሏል

👉 21 ነጥብ 23 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያላቸው 437 አልሚ ባለሀብቶች ለልማት ተመርጠዋል

👉 20 ሚሊዮን ብር ተመድቦ የግብርና እና የኢንዱሥትሪ ምርቶችን በማቅረብ የገበያ ማረጋጋት ሥራም ተሠርቷል

👉 የሕገወጥ የሸቀጦች ዝውውር ቁጥጥር ሥራም ተከናውኗል

👉 የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም ተጨማሪ ዳቦ ቤቶች መከፈታቸውን እና 20 ሚሊዮን ብር ለሸማች ማኅበራት ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል።

ሪፖርቱን ያዳመጡት የምክር ቤት አባላት በሪፖርቱ መነሻነት አስተያየት ሰጥተዋል። አባላቱ በሰጡት አስተያየት እንዳሉት፡-

👉 በከተማው የጸጥታ እና የዘረፋ ችግርን ለመቀነስ በትኩረት መሠራት ይገባዋል

👉 በመልካም አሥተዳደር ብልሽት ሕዝቡን የሚያንገላቱ አመራሮች ላይ የሚወሰደው እርምት ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል

👉 ካሣ የተከፈለባቸውን መሬቶች መረጃ ለይቶ በመያዝ ከብልሹ አሠራር እንዲነጹ ማድረግ ይገባል

👉 ሕገ ወጥ ግንባታ እየተከናወነ በመኾኑ ደንብ የማስከበር ሥራን ከቦታው በመገኘት መሥራት ያስፈልጋል

👉 የሥራ አጥ ቁጥር መበራከት ለወንጀል መበራከት ምክንያት በመኾኑ አሁንም መፍትሄ ያሻዋል

👉 በኑሮ ውድነቱ ምክንያት ለጎዳና እና ልመና የተዳረጉ ሰዎች በመብዛታቸው የምገባ ማዕከሎች ቢከፈቱ

👉 ተጨማሪ የሕዝብ መድኃኒት ቤቶች ቢከፈቱ ሲሉ አንስተዋል።

ዘጋ:- ዋሴ ባየ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየተፈጠረው የፀጥታ ችግር የትምህርት ዘርፉን እየጎዳው መኾኑን የሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።
Next articleበማኅበረተሰቡ የሚነሱ ጥያቄዎችን በየደረጃዉ እንደሚፈታ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ፡፡