የተፈጠረው የፀጥታ ችግር የትምህርት ዘርፉን እየጎዳው መኾኑን የሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።

72

ደብረ ብርሃን: ኅዳር 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ሸዋ ዞን ከሚገኙ 1 ሺህ 21 የትምህርት ተቋማት ውስጥ የመማር ማስተማር ሥራውን እያካሄዱ ያሉት 725 ትምህርት ቤቶች ብቻ መኾናቸውን የዞኑ ትምህርት መምሪያ ምክትል ኀላፊ ታደሰ ሸዋፈራ ገልጸዋል።

በዞኑ ውስጥ ከ69 በመቶ በላይ የሚኾኑት ተማሪዎች ዕድሜያቸው እስከ 12 ዓመት የደረሱ መኾናቸውን የገለጹት ምክትል መምሪያ ኀላፊው ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ መቸገራቸውንም ተናግረዋል።

በዞኑ ከተመዘገቡት 217 ሺህ ተማሪዎች ውስጥ 135 ሺህ ተማሪዎች ብቻ ወደ ትምህርት ቤት መሄድ እንደቻሉም አስገንዝበዋል።

በዞኑ የሚገኙ አራት ወረዳዎች ደግሞ ትምህርት ያልጀመሩ ሲኾን ምንም ዓይነት ምዝገባ ያላከናወኑ ሦስት ትምህርት ቤቶች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።

የፀጥታ ችግር ቢኖርም ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ተቋማት ማምጣት ወሳኝ በመኾኑ ከወረዳ እና ከተማ አሥተዳደር የትምህርት ባለ ድርሻ አካላት ጋር የጋራ መድረክ መፈጠሩን ነው አቶ ታደሰ የተናገሩት።

አሚኮ ያነጋገራቸው የወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊዎች እና ባለሙያዎች የፀጥታ ችግሩ ከምዝገባ ጀምሮ ተፅዕኖ እያሳደረ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

ከማኅበረሰቡ ጋር በመነጋገር ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ለማምጣትም ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡- በላይ ተስፋዬ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከ10 ሚሊዮን በላይ መጻሕፍት ለክልሎች እና ከተማ አሥተዳደሮች ተከፋፍሏል” ትምህርት ሚኒስቴር
Next articleየሥራ አጥ ቁጥር መበራከት ለወንጀል መበራከት ምክንያት በመኾኑ አሁንም መፍትሄ እንደሚያሻው የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት አባላት ተናገሩ፡፡