“ከ10 ሚሊዮን በላይ መጻሕፍት ለክልሎች እና ከተማ አሥተዳደሮች ተከፋፍሏል” ትምህርት ሚኒስቴር

66

ባሕር ዳር: ኅዳር 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲሱን ሥርዓተ ትምህርት ትግበራ ተከትሎ ከ22 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ የሁለተኛ ደረጃ የመማሪያ ማስተማሪያ መጸሕፍት መታተማቸው ተገልጿል።

በትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ ከታተሙ መጻሕፍት ውስጥ ከ10 ሚሊዮን በላይ የሚኾኑትን ለክልሎች እና ለከተማ አሥተዳደሮች ማከፋፈል መቻሉን ተናግረዋል።

የመምህራን እና የትምህርት የሥራ ኀላፊዎችን አቅም ለማጎልበት የሚያስችል ገዢ መመሪያን የማሻሻል ሥራ መጀመሩንም አንስተዋል።

በ”ትምህርት ለትውልድ” ንቅናቄ በጦርነት የወደሙ፣ ከደረጃ በታች ያሉ ትምህርት ቤቶችን ለማሻሻል እና ለመገንባት ኅብረተሰቡን እና ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ከፍተኛ ርብርብ መደረጉንም ገልጸዋል።

የኅብረተሰቡን ተሳትፎ በማጎልበት በትምህርት ዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን ለመቅረፍ በትኩረት መሥራት እንደሚያስፈልግ ሚኒስትር ዴኤታዋ አሳስበዋል።

32ኛው የትምህርት ጉባኤ በጅግጅጋ እየተካሄደ ሲኾን ውጤታማ ተግባራትን ለማስቀጠል እና ተግዳሮቶች ላይ በመወያየት የጋራ መፍትሔ ለማስቀመጥ ያግዛል ተብሏል።

የመማሪያ ማስተማሪያ መጻሕፍት እጥረት፣ የመምህራን እና የትምህርት የሥራ ኀላፊዎች አቅም ማነስ፣ የምገባ መርሐ ግብር በተፈለገው ልክ አለመከወን፣ ልዩ ፍላጎት ያላቸው ዜጎች የትምህርት ተሳትፎ ማነስ እና የተማሪዎች ውጤት ዝቅተኛ መኾን የትምህርት ዘርፋ ቁልፍ ችግሮች መኾናቸው ተጠቅሷል።

በጉባዔው የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች፣ የክልሎች እና የከተማ አሥተዳደሮች የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት እና መልካም ተሞክሮዎች ቀርበው ውይይት ይካሄድባቸዋል ተብሏል።

ኢቢሲ እንደዘገበው የትምህርት ሚኒሥትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ፣ የክልል የትምህርት ዘርፍ የሥራ ኀላፊዎች እና ባለድርሻ አካላትም እየተሳተፉበት ነው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ 180 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመገንባት ጨረታ ወጥቷል” የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን
Next articleየተፈጠረው የፀጥታ ችግር የትምህርት ዘርፉን እየጎዳው መኾኑን የሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።