
ባሕር ዳር: ኅዳር 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ በሀገሪቱ ከሚገኙ 13 ብሔራዊ ፓርኮች መካከል አንዱ ነው። ፓርኩ በርካታ የአዕዋፍት እና የእንስሳት ዝርያዎችን በውስጡ ይዟል። ከፍተኛ የደን ሽፋን ያለው ፓርክም ነው።
በኢትዮጵያ በመጥፋት ላይ የሚገኙ እና አዋጅ ወጥቶላቸው በልዩ ጥበቃ ላይ የሚገኙ፤ ከፍተኛ ምጣኔ ሃብታዊ ጠቀሜታ ያላቸው በርካታ የእጽዋት ዝርያዎችን ጭምር በውስጡ ይዟል። የበርሃማነት መስፋፋት እና የካርቦን ልቀትን ከሚከላከሉ የሀገሪቱ ሥነ ምህዳር መካከልም ተጠቃሽ ነው። የሙቀት መጠኑ እስከ 41 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ይደርሳል።
በቱሪዝም ዘርፉ ከፍተኛ ምጣኔ ሃብታዊ ፋይዳ እንደሚያስገኝ የታመነበት ይህ ፓርክ በተገቢው መንገድ ባለመልማቱ መገኘት የሚገባውን ጥቅም ማግኘት አለመቻሉን የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ ኀላፊ ሙላው ሽፈራው ነግረውናል። ኀላፊው እንዳሉት የፓርኩን ስፉት የሚመጥን የመንገድ መሠረተ ልማት ባለመሟላቱ በሁሉም አካባቢ በቀላሉ ተንቀሳቅሶ የሚፈጸሙ ሕገ ወጥ ድርጊቶችን ለመቆጣጠር ፈታኝ አድርጎታል።
በአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ የሚፈስሱ ወንዞች በበጋ ወራት ዘላቂ ባለመኾናቸው እንስሳት ውኃ ፍለጋ ወደ ሱዳኑ የዲንደር ፓርክ ይሸሻሉ። በፓርኩ ውስጥ በበጋው ወራት የሚያጋጥመውን የእንስሳት ፍልሰት ለመከላከል የአይማን ወንዝ 10 ኪሎ ሜትር በመቁረጥ ወደ ፓርኩ ውስጥ እንዲፈስስ ለማድረግ ጥያቄውን በዚህ ዓመት መጀመሪያ ለኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን አቅርበው “ለገንዘብ ሚኒስቴር ይቀርባል” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።
የአይማንን ወንዝ መቁረጥ ከተቻለም የዱር እንስሳትን ፍልሰት ከመከላከል ባለፈ በየጊዜው የሚነሳውን ሰደድ እሳትም በቀላሉ መከላከል ይቻላል። የፓርኩንም ብዝኃ ሕይዎት ዘላቂነትም ማረጋገጥ ይቻላል ብለዋል።
ዘርፉን ለማልማት የመንግሥት፣ የግል ተቋማት እና በብዝኃ ሕይዎት ላይ የሚሠሩ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። የሚዲያ ተቋማትም የማስተዋወቅ ሥራ እንዲሠሩ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ፓርኮች አሥተዳደር ዋርደን መኳንንት ክንፈ እንዳሉት በአልጣሽ ብሔራዊ ፖርክ 180 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ደረጃውን የጠበቀ የጠጠር መንገድ ለመሥራት ጨረታ ወጥቷል።
ተቋራጮችም በጨረታው ለመወዳደር መንገዱ የሚሠራበትን አካባቢ የቅድመ ጥናት ሥራ እየሠሩ መኾኑን ገልጸዋል። በዚህ ዓመትም ሥራ እንደሚጀመር ነው የተገለጸው።
የመንገድ ሥራው ታኅሣሥ ከተሠኘው አካባቢ እስከ አምዶክ፣ ከመግቢያ በር እስከ ኦሜድላ እና ከጃቫ እስከ አልጋ ያሉ ቦታዎችን ለማገናኘት የታሰበ እንደኾነ አቶ መኳንንት ገልጸውልናል።
የመንገድ ሥራው ከተጠናቀቀ በፓርኩ የሚነሳውን ሰደድ እሳት እና ማንኛውም ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ በቀላል መንገድ እና በፍጥነት ቅኝት ለማድረግ እና ለመቆጣጠር ያስችላል ብለዋል። ድንበር ተሻጋሪ ሕገ ወጥ ድርጊቶችንም ከሱዳን መንግሥት ጋር በመተባበር ለመቆጣጠር ያግዛል። ባለሃብቶችም በፓርኩ እንዲያለሙ ያስችላል።
የአይማ ወንዝን ወደ ፓርኩ እንዲፈስስ ለማድረግ የቀጣይ የእቅድ አካል ኾኖ እንዲያዝ ባለሥልጣኑ ይሠራል ብለዋል።
የአልጣሽ ፓርክ በብዝኃ ሕይዎቱ አቅም ያለው ፓርክ መኾኑን ያነሱት አቶ መኳንንት በቀጣይ የተጠናከረ ጥበቃ ለማድረግ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። የፓርኩ ልማት ለአንድ ተቋም ብቻ የሚተው ሳይኾን ክልሉ፣ በብዝሃ ሕይዎት ላይ የሚሠሩ ድረጅቶች እና ግለሰቦች ከባለሥልጣኑ ጋር በመተባበር በጋራ እንዲሠሩም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!