“በፍርድ ቤቶች ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን ሊቀርፍ የሚችል የሕግ ማሻሻያ ሊደረግ ነው” ጠቅላይ ፍርድ ቤት

75

ባሕር ዳር: ኅዳር 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ተገልጋዮች በፍርድ ቤቶች ላይ የሚያነሷቸውን ቅሬታዎች ለመቅረፍ፣ የዳኝነት አገልግሎት ተጠያቂነት ለማስፈን እና የዳኝነት አካል ሥልጣንን የሚሸረሽሩ ሕጎችን ለመከለስ የሚያስችል የሕግ ማሻሻያዎችን ለማድረግ መዘጋጀቱን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ገልጿል፡፡

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ስትራቴጂክ ዳይሬክተር አቤል ጌትነት ፍርድ ቤቶች ያልተሻገሯቸውን ችግሮች ለማለፍ እንዲኹም የፍርድ ቤት አሠራርን፣ ቅልጥፍናን እና ውጤታማነትን ለማሳደግ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የለውጥ ፍኖተ ካርታ ወጥቷል፡፡

የፍኖተ ካርታው ዋነኛ ዓላማ ተገልጋዮች በፍርድ ቤቶች ላይ የሚያነሷቸውን ችግሮች እና ቅሬታዎች መቅረፍ፣ የዳኝነት አገልግሎት ተጠያቂነትን ማስፈን እንዲኹም በዳኝነት ነፃነት እና ተጠያቂነት መካከል ያሉ ሚዛኖችንም አስጠብቆ ለመሔድ የሚያስችል መኾኑን ጠቁመዋል፡፡

ፍኖተ ካርታው የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን በክልሎች ለማደራጀት የሚጠይቅ እና የበጀት አሥተዳደር ነፃነት ችግር ለመፍታት የሚያስችል መኾኑም ተመልክቷል፡፡

የበጀት አሥተዳደር ነፃነት ችግር፣ የዳኝነት ውሳኔዎችን አለማክበር፣ በተገልጋይ እና አገልግሎት ሰጪዎች መካከል አልፎ አልፎ ያልተገቡ ግንኙነቶች መኖር እንዲኹም በግልጽ ችሎት አለማስቻል ፍርድ ቤቶች ያልተሻገሯቸው ችግሮች መኾናቸው በፍኖተ ካርታው መመላከቱን አቶ አቤል ተናግረዋል፡፡

ውጤታማነትን የሚቀንሱ አሠራሮችን ፈትሾ ማስተካከል፣ የውዝፍ መዛግብት መቀነሻ ስትራቴጂ አዘጋጅቶ ለመተግበር መታቀዱንም ጠቁመዋል፡፡ በተገልጋዮች ዘንድ በቅሬታ የሚያስነሳውን የመዝገቦች አያያዝ ችግር ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ለማስተካከል በለውጥ ርምጃው ትኩረት ተሰጥቷልም ነው ያሉት፡፡

በለውጥ ፍኖተ ካርታው ግልጽነትን ማረጋገጥ፣ የላቀ እና ውጤታማ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማሳደግ፣ ቅንጅታዊ አሠራርን ማጠናከር እና ተደራሽነትን ማሥፋት ትኩረት የተሠጠው መኾኑንም ተናግረዋል፡፡

በጥራት በኩልም ትእዛዞች፣ ብይኖች እና ውሳኔዎች ግልጽ፣ ወጥ እና ተገማች አለመኾን በፍርድ ቤቶች አሁንም እንደሚስተዋል በፍኖተ ካርታው የተለዩ ችግሮች መሆኾቸውን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ የሀሰተኛ ማስረጃዎች መበራከት እና የጥራት ስታንዳርድ አለመኖር ችግር ፈተና መኾኑን አንስተዋል፡፡

ከተጠያቂነት አኳያም የሙስና መከላከል እና መቆጣጠር ስትራቴጂ ደንብ ትግበራ ዳሰሳ ጥናት እንደሚካሔድ እና የዳኝነት አገልግሎት ጥራት ማረጋገጥን መሰረት እንደሚያደርግም ነው የተናገሩት፡፡

የሕዝብን አመኔታ ያተረፈ፣ ቀልጣፋ፣ ጥራት ያለው የዳኝነት አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም ለመፍጠር የሚያስችል ውጤት የሚያስገኝ መኾን እንዳለበትም ተጠቁሟል፡፡ በኅብረተሰቡ ዘንድ ነፃ እና ገለልተኛ ኾኖ መገኘት፣ ወጥ እና ተገማች አገልግሎት መሥጠት የሚያስችል የዳኝነት አገልግሎት ስታንዳርድ ይዘጋጃል ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡

አቶ አቤል ለኢፕድ እንደገለጹት ፍኖተ ካርታው በዘርፉ አገልግሎት አሰጣጥ ግልጽ፣ ቀልጣፋ እና ተደራሽ ማድረግን ታሳቢ ማድረጉንም አመልክተዋል፡፡ ውዝፍ መዝገቦች የዳኝነት አገልግሎቱ አንድ ተግዳሮት መኾናቸው፣ መዝገቦችን የማጥራት ምጣኔን ማሳደግ ላይም ትኩረት ተሰጥቷል፡፡ የተገልጋዮችን ቅሬታ እና ለአገልግሎቶች ቀልጣፋ ምላሽ መሥጠት ትኩረት ያደረገ ዓላማ መሰነቁም ተቀምጧል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔ ተጀምሯል።
Next article“በአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ 180 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመገንባት ጨረታ ወጥቷል” የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን