
ባሕር ዳር: ኅዳር 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አብዲ ዘነበ (ዶ.ር) በሩብ ዓመቱ 63 ሺህ 81 መንገደኞችን ማስተናገዱን ገልጸዋል። 587 ሺህ ቶን የገቢና ወጪ ጭነት በማጓጓዝ 998 ነጥብ 13 ሚሊዮን ብር ገቢ አግኝቷል ነው ያሉት።
በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 875 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ገቢው ከዕቅድ በላይ ማሳካት መቻሉን አስረድተዋል።
በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 670 ሺህ ቶን ገቢና ወጪ ጭነት ለማጓጓዝ ታቅዶ 587 ሺህ ቶን ተጓጉዟል ነው ያሉት ዶክተር አብዲ። በተጨማሪም 37 ሺህ 500 መንገደኞችን ወደ ተለያዩ መዳረሻዎች ለማጓጓዝ ታቅዶ 63 ሺህ 081 በማጓጓዝ ከዕቅድ በላይ ማሳካት ተችሏል ብለዋል።
ዶክተር አብዲ እንዳመለከቱት የባቡር መስመሩ በ20 ጣቢያዎች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። በቀጣይም አገልግሎት መስጫ አዳዲስ ጣቢያዎችን ለመክፈት ዝግጅት እየተደረገ ነው።
ድርጅቱ በድሬዳዋ፣ በሞጆ፣ በአዳማ፣ በለቡ፣ በእንዶዴ፣ በዲኬና በመኢሶ እንዲሁም በደወሌ የባቡር ጣቢያ መስመሮች የጭነትና የመንገደኞች የባቡር አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ዶክተር አብዲ ተናግረዋል።
የተማሪዎች የመማሪያ መጽሐፍትና የአፈር ማዳበሪያ በኢትዮ ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አማካኝነት እየተጓጓዙ መሆኑን አስታውቀዋል። የተለያዩ ተሽከርካሪዎች፣ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የተለያዩ ምርቶችን የማጓጓዝ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።
በቀጣይም ሲሚንቶና አሸዋ በባቡር ለማጓጓዝ ዕቅድ ተይዟል ብለዋል። ለዚህ የሚረዳ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።
እንደ ዶክተር አብዲ ገለጻ ተቋሙ በአጠቃላይ ጭነት የማጓጓዝ አቅሙን ከአንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ቶን ወደ ሁለት ሚሊዮን ቶን ከፍ ማድረግ ተችሏል።
ድርጅቱ የጭነት ወጪን በመቀነስ ለተለያዩ ተቋማት ውጤታማ አገልግሎት እያቀረበ ነው ያሉት ዶክተር አብዲ ከጥር ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ በስድስት ወራት ውስጥ ከሦስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታውሰዋል።
ኢፕድ እንደዘገበው እስከ 2016 ዓ.ም ታኅሣሥ ወር መጨረሻ ድረስ ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
የባቡር መስመሩ ኢትዮጵያና ጂቡቲን በማገናኘት ከወደብ ወደ መሀል ሀገር የተለያዩ ሸቀጣሸቀጦችን በማጓጓዝ ለትራንስፖርት ዘርፉ ዕድገት ከፍተኛ ድርሻ እያበረከተ እንደሚገኝ ታውቋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!