
ባሕር ዳር: ኅዳር 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዛሬው መርሐ ግብር የአስቶንቪላ እና ቶተንሃም ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በዛሬ ውሎው ቶተንሃምን ከአስቶን ቪላ 11:00 ሲያገናኝ ፤ ኤቨርተን ከማንቸስተር ዩናይትድ ደግሞ ምሽት 1:30 ላይ ይጫወታሉ፡፡
የቶተንሃም እና የአስቶን ቪላ ጨዋታ ከደረጃቸው አንጻር በእጅጉ አጓጊ ኾኗል፡፡
ቶተንሃም በዚህ የውድድር ዘመን በ12 ጨዋታዎች ስምንቱን አሸንፎ በሁለቱ አቻ ወጥቶ በሁለቱ ደግሞ ተሸንፎ በ26 ነጥብ በአራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
አስቶን ቪላ በበኩሉ 12 ጨዋታዎችን አድርጎ በስምንቱ ማሸነፍ ችሏል፡፡ በሦስቱ ደግሞ ተሸንፎ በአንዱ አቻ ተለያይቶ በ25 ነጥብ አምስተኛ ነው፡፡
በሁለቱ ቡድኖች መካከል ያለው የነጥብ ልዩነት አንድ ብቻ ነው፡፡ ስለኾነም ጨዋታውን ማሸነፍ በሁለቱ ቡድኖች ዘንድ የደረጃ ለውጥ ያመጣል፡፡ ቶተንሃም ካሸነፈ ደረጃውን ወደ ሦሥት ከፍ ያደርጋል፡፡ አስቶን ቪላም ድል የሚቀናው ከኾነ ደረጃውን ወደ አራት ያሳድጋል፡፡
የቶተንሃም አሠልጣኝ አንጂ ፖስትኮግሉ “ወሳኝ ተጫዋቾቼ ጉዳት ላይ ናቸው፤ ይሁንና ህመማቸውን ተቋቁመው በመጫወት ለማሸነፍ ተዘጋጅተዋል” ብለዋል፡፡
አሠልጣኙ አክለውም ለአስቶን ቪላ ዝቅተኛ ግምት ሰጥተን ወደ ሜዳ አንገባም፤ በተለይ ደግሞ በሜዳችን በመጫወታችን መዘንጋት የለበትም፤ ቡድኔ እየተዘጋጀ ያለው ዋንጫ ለመውሰድ ስለሆነ እናሸንፋለን ብለዋል፡፡
የአስተን ቪላው አለቃ ኡናይ ኢሜሪ በበኩላቸው ጉዳት አጋጥሞት የነበረው ጆን ማክጊን ለጨዋታው ይደርሳል፤ግብ ጠባቂው ኤሚልያኖ ማርቲኔዝም ብቁ ነው ብለዋል፡፡
በሌላኛው ጨዋታ ኤቨርተን እና ማንቸስተር ዩናይትድ ምሽት 1:30 ይገናኛሉ።
ኤቨርተን በታሪኩ ማንቸስተር ዩናይትድን በ71 ጨዋታዎች አሸንፎታል፡፡ ሁለቱ ቡድኖች በተገናኙባቸው 47 ደግሞ ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል፡፡
ማንቸስተር ዩናይትድ ደግሞ ኤቨርተን በ93 ጨዋታዎች ረትቶታል፡፡
ኤቨርተን በእንግሊዝ እግርኳስ ማኅበር የ10 ነጥብ ቅጣት ከተጣለበት በኋላ የሚያከናውን ነው ጨዋታ መኾኑን ቢቢሲ አስነብበቧል።
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!