
ባሕር ዳር: ኅዳር 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ አፄ ቴዎድሮሥ ክፍለ ከተማ ለከተማ አርሶ አደሮች እና ተቋማት የመሬት ይዞታ ማረጋጫ ደብተር ሠጥቷል።
አርሶ አደር በሬ እንቢአለ በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የአፄ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ናቸው። የመሬት ባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር ባልነበራቸው ጊዜ ለተለያዩ አገልግሎቶች የመሬት ባለቤትነት ደብተር ስለሚጠየቁ ብዙ ይቸገሩ እንደነበር ገልጸዋል። ”የባለቤትነት ደብተር በማግኘታችን ችግራችን ይቃለላል” ሲሉም አመሥግነዋል።
”የባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር ባልነበረን ጊዜ በመሬታችን ላይ ማዘዝ አንችልም ነበር፤ ተቀናቃኝ ቢመጣ ወደ ሕግ ብንቀርብ የባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር አምጡ እንባል ነበር። አሁን ግን ደብተሩን በማግኘታችን በርካታ ጥቅም እናገኛለን” ያሉት ደግሞ በባሕርዳር ከተማ የአፄ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ ነዋሪው መላእከ ብርሃን ፍስሐ ጥላሁን ናቸው።
ለልጆቻቸው መሬት ለመስጠትም ኾነ ብድር ለማግኘት የባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተሩ እንደሚያግዛቸው ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የተናገሩት።
የባሕርዳር ከተማ መሬት መምሪያ ኀላፊ መልካምሥራ ካሣው በባሕር ዳር ከተማ በስድስቱም ክፍለ ከተሞች የመሬት ባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተርን ለመሥጠት አሥፈላጊውን ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል። የአፄ ቴዎድሮሥ ክፍለ ከተማ 820 ባለይዞታዎችን ጨምሮ እስካሁን በሦስት ክፍለ ከተሞች 1 ሺህ 231 ባለይዞታዎች የመሬት ባለቤትነት ደብተር መሰጠቱን ገልጸዋል። ሕገ ወጥ የመሬት ባለቤትነት ደብተሮችን እንዲመክኑ መደረጉን ተናግረዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳዳር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ለባለይዞታዎች የተሰጠው የባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር በሕጉ መሰረት እንዲጠቀሙ አሳስበዋል። ባለይዞታዎች መሬቱን በአግባቡ እንዲያለሙም መክረዋል፡፡ ቦታው ለላቀ ልማት በተፈለገ ጊዜ ተገቢውን ካሳ የሚያገኙበትን አስተማማኝ የባለቤትነት ደብተር መኾኑንም ጠቅሰዋል፡፡
እስካሁን ለሦስት ክፍለ ከተሞች የባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር መሠጠቱን እና ለቀሪ ክፍለ ከተሞችም በቀጣይ እንደሚሠጥ ገልጸዋል፡፡
”ቃል በገባነው መሰረት የሕብረተሰቡን ጥያቄ እየመለስን ነው” ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የሰላም ጉዳይ የሁላችን ስለኾነ ሁሉም ለሰላም ዘብ ይቁም ሲሉ አሳስበዋል።
በሥነ ሥርዓቱ የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ እብሬ ከበደ፣ የባሕር ዳር ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሞላ ሁሴን እና የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳዳር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስራቴ ሙጨን ጨምሮ ሌሎች የባሕር ዳር ከተማ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ:- ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!