“አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ስንል ትኩረታችን ቴክኖሎጂው የሚያከናውነው ተግባር ላይ ነው” የቴክኖሎጂ ባለሙያ ሰለሞን ካሳ

58

ባሕር ዳር: ኅዳር 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሶፍትዌር መሐንዲሶች እንደሚገልጹት አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኮምፒዩተሮች እና ማሽኖች እንደ ሰው ልጅ እንዲያመዛዝኑ፣ ነገሮችን እንዲገነዘቡ፣ ማንኛውንም ነገር እንዲማሩ፣ እንዲያቅዱ እና ፈጠራዎችን እንዲከውኑ በማድረግ የሚሰጣቸውን ተልዕኮ እንዲያሳኩ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው።

በአፍሪካ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ እና ግብፅ ለአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ትኩረት ሠጥተው መሥራት ከጀመሩ ሰንብተዋል። ኢትዮጵያም ከሦስት ዓመታት ወዲህ ቴክኖሎጂውን ለማሳደግ ደፋ ቀና ማለት ጀምራለች።

ወጣቱ የቴክኖሎጂ ባለሙያ ሰለሞን ካሳ እንደሚናገረው ዓለማችን አራት የቴክኖሎጂ ወይም የኢንዱስትሪ አብዮት አስተናግዳለች። የመጀመሪያው ከሁለት መቶ ዓመታት በፊት ሌሎቹ ደግሞ ከዚያ መልስ የተስተናገዱ ናቸው። አራቱ አብዮቶች ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ አፍሪካውያንን አምልጠዋቸዋል።

ሰሎሞን እንደሚለው አሁን ባለንበት ዲጂታል በሚባለው የቴክኖሎጂ ዘመን ማዕከላዊ ቦታ ይዞ እየዘወረ ያለው አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ነው። ይሔ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ከግንዛቤ ገብቷል። በምንም ዓይነት መልኩ ቴክኖሎጂውን ወስደን ለራሳችን በሚጠቅም ሁኔታ መጠቀሙ ምርጫ ሳይኾን ግዴታ እንደኾነ በሀገር ደረጃ መረዳቱ እና ፍላጎቱ አለ።

«እኔ እንደ ቴክኖሎጂስት ሁልጊዜም ቴክኖሎጂው ላይ እንድናተኮር አልፈልግም። ቴክኖሎጂ እንደ መዶሻ እና ፒንሳ ያለ መሣሪያ ነው። በዚያ መሣሪያ ምን ዓይነት ፕሮጀክት መሥራት እንችላለን ብለን ነው መጠየቅ ያለብን» የሚለው ወጣቱ ቴክኖሎጂስት፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ስንል ነገርየው አይደለም ትኩረታችን ዋናው ጉዳይ ቴክኖሎጂው የሚያከናውነው ነገር ነው ይላል።

አያይዞም አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ምን ያደርግልናል? ሀገራችን ላይ ያለውን ችግር ለመቅረፍ እንዴት ያግዘናል ብለን ነው መጠየቅ ያለብን። በእርሻ፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በመልካም አሥተዳደር እና በአጠቃላይ ወሳኝ በኾኑት ነገሮቻችን ላይ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን እንደ አንድ መሣሪያ ለመጠቀም መንቀሳቀስ አለብን ሲል ይመክራል።

አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዕድሜን እንደሚቀጥል፣ ከውድቀት እንደሚታደግ፣ የምግብ ዋስትናን እንደሚጨምር እና በርካታ ሌሎች በረከቶች እንዳሉት ገልጿል ሰለሞን።

ሰሎሞን እንደሚለው “መሠረታዊ በምንላቸው ዘርፎች ላይ ሁሉ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስን በረከት መጠቀም ይኖርብናል። ሁሉም ቴክኖሎጂ በጎም በጎ ያልሆነም ጎን ስላለው በታዳጊዎች ላይ የቴክኖሎጂውን በጎ ጎን ማስረጽ ይገባል” ሲል ያሳስባል።

ኢትዮጵያ ከቴክኖሎጂው በረከቶች ለመቋደስ እየሠራች በምትገኘው ሥራ ላይ ያለውን ግምገማ ሲያስቀምጥም “የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቱቲዩት ሀገራችን ከቴክኖሎጂው በትክክል መጠቀም በምትችልባቸው ጉዳዮች ላይ እየሠራ ነው። ኢንስትቲዩቱ ከተመሠረተ ሦስት ዓመት ያስቆጠረ ጨቅላ ቢኾንም የአርባ እና ሃምሳ ዓመት ዕድሜ ያለው ተቋም የሚሠራውን ሥራ እየሠራ ነው የሚገኘው” ብሏል።

ተቋሙ ሲመሠረት ጀምሮ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ.ር) እጅ እንደነበረበት አመልክቷል፡፡ በቀጣይነት ከፍተኛ ሥራ እንዲሠራ ጠንካራ ክትትል እየተደረገለት እንደሚገኝ መረዳታቸውን ተናግረዋል።

እንደ አቶ ሰሎሞን ማብራሪያ ቴክኖሎጂ እንደሌላው ዘርፍ ቆሞ የሚጠብቅ አይደለም ፍጥነት ይፈልጋል። ዛሬ ሠራሁና አበለጽግኩ ብሎ መኩራራትን እና መቆምን አይፈቅድም። ዛሬ አዲስ የኾነው ቴክኖሎጂ በማግሥቱ በተሻለ ተተክቶ ይገኛል። የዘመኑን ቴክኖሎጂ መከተል የሚያስችል ቁመና ያለው እንደ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስትቲዩት ዓይነት ተቋም ያሥፈልጋል።

ወጣቱ ቴክኖሎጂስት ኢትዮጵያ ከአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በፊት ትኩረት ልትሰጣቸው የሚገባቸው ሌሎች አንገብጋቢ ጉዳዮች አሏት በሚል ከተቺዎች የሚደመጠውን አስተያየት “ኢትዮጵያ ለቴክኖሎጂው ገና ነች መባል የለበትም። ገና ነን ስንል አምስተኛው የቴክኖሎጂ አብዮት ፈንድቶ ያመልጠናል። ያ ደግሞ ወደ ኋላ መቅረቱን ይበልጥ እያሠፋው ይሄዳል” ሲል አጣጥሎታል።

የሕግ ጠበቃ እና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም በበኩላቸው አሁን ዓለም የያዘችው መንገድ ወደ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እያመራ ያለ ነው። ብዙ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ተመራማሪዎች እና ፈላስፋዎች እንደሚሉት የሰው ልጅ እጅግ ወሳኝ የኾነ ጊዜ ላይ ነው የሚገኘው። አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በተያያዘው መንገድ ከቀጠለ ሰውን የመተካት ችሎታ አለው ይላሉ።

አካባቢያችንን ላንገነዘበው ወይም ላናውቀው እንችል ይኾናል እንጂ ባለንበት ዘመን ሁሉ ነገር አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ነው የሚሉት ፕሮፌሰሩ ”ራሳቸውን የሚያሽከረክሩ መኪናዎች ጎዳና ላይ የወጡበት ዘመን ነው። የትም ቦታ ብንሄድ ማሽኖች ከሰው ልጅ ጋር ተግባብተው አገልግሎቶችን ሲሰጡ እንመለከታለን። አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዓለምን ተቆጣጥሯል። ግን ልብ አንለውም” ይላሉ።

አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በየቀኑ በአስገራሚ ፍጥነት እያደገ በመሄዱ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሥራ ላይ ባለው የሕግ ማዕቀፍ መዳኘት የማይችልበት ደረጃ ይደርሳል የሚል ተጨባጭ ስጋት በመኖሩ አሜሪካን ሀገር ራሱን የቻለ ሕግ ይውጣለት እየተባለ መኾኑን ጠቁመዋል። “በኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ለኅብረተሰባችን የሚሰጠውን ጥቅም እና ሊያመጣ የሚችለውን ጠንቅ በተመለከተ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ምሁራን ተሰባስበን ልንመክርበት ይገባል” ሲሉ ጥሪ ያቀርባሉ።

“ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ.ር) አርቆ አሳቢ ስለኾኑ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በሀገር እድገት ላይ የሚኖረውን ሚና ዛሬ ሳይኾን ከዛሬ 10 እና 15 ዓመታት በፊት የተረዱ ናቸው፤ በጉዳዩ ላይም ጽፈዋል» ያሉት የሕግ-ጠበቃና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ፣ ኢትዮጵያ ለአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ልዩ ትኩረት ሰጥታ መሥራቷ ቅንጦት የሚመስላቸው አካላት ተሳስተዋል ይላሉ።

“በትምህርት ሥርዓታችን ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ አንድ ይዘት ኾኖ መካተት አለበት። ታዳጊዎችን በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ማሠልጠን ጥይት የጎረሰ ጠብመንጃ እንደመሥጠት ስለኾነም ለበጎ ነገር እንዲጠቀሙት አድርገን ማስረጽ አለብን” ነው ያሉት። ፕሮፌሰር አለማየሁ የኢትዮጵያ ወጣቶች ወደ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ አዘንብለው ሀገሪቷን በከፍተኛ ደረጃ ይረዳሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

ኢፕድ እንደዝርገበው አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዓለማችንን የተዋወቀው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1956 ነበር። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአሁኑ ወቅት አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በዓለማችን ኢኮኖሚ ውስጥ ያለው ድርሻ ከ350 ቢሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል። በቀጣይም በሁሉም መስኮች ተጽዕኖው እየበረታ እንደሚሄድ ይጠበቃል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአዲሱን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለማጠናከር ሀገር ዓቀፍ የገቢ ማሰባሰቢያ መርኃ ግብር በአዲስ አበባ እተካሔደ ነው።
Next articleየባሕር ዳር ከተማ አሥተዳዳር ለ820 ባለይዞታዎች የመሬት ባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር መሥጠቱን አስታወቀ፡፡