
ባሕር ዳር: ኅዳር 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በ2016 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከውጭ ጎብኝዎች ብቻ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ቱሪዝም ሚኒስቴር ገልጿል። ከሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ደግሞ ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱ ተነግሯል። በዘርፉ ለ17 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩም ተጠቁሟል፡፡
የሚኒስቴሩ የኮሙኒኬሽን እና የሕዝብ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ አለማየሁ ጌታቸው በበጀት ዓመቱ የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማነቃቃት በርካታ ሥራዎች መከናዎናቸውን አንስተዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት ከሀገር ውስጥ ጎብኚዎች 68 ቢሊዮን ብር ለማግኘት መታቀዱን አመልክተዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከስምንት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን በላይ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ጎብኝተዋል፡፡
በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከ280 ሺህ በላይ የውጭ ቱሪስቶችን በማስተናገድ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱ አቶ አለማየሁ ገልጸዋል፡፡
ከሀገር ውስጥ የተገኘው ገቢ በቱሪዝም ኢንዱስትሪ ዘርፍ በሚገኙ አስጎብኚ ድርጅቶች፣ ሆቴሎች፣ ባሕላዊ ቁሳቁስ ሻጮች እና መሰል አገልግሎት ሰጪዎችን ተጠቃሚ ያደረገ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን እንቅስቃሴ እና ፍስሰት ለመጨመር ከፍተኛ ሥራ የተሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡ ከዚህም በሳይንስ ሙዚየም በተዘጋጀው አውደ ርዕይ ከ159 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ሰዎች በሀገሪቱ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ማስተዋወቅ መቻሉንም አውስተዋል፡፡ ይህም የዜጎች የቱሪዝም መዳረሻዎችን የመጎብኝት ባሕል እያደገ እንዲሔድ የበኩሉን ሚና እንደሚጫወትም ገልጸዋል፡፡
እያደገ የመጣው የዘርፉን ኢንቨስትመንት ከማስፋፋት አንጻር በሩብ ዓመቱ 46 የሀገር ውስጥ እና 11 የውጭ ባለሀብቶች በሆቴል እና መሰል አገልግሎት ዘርፍ መቀላቀላቸውን ጠቁመዋል፡፡
በሩብ ዓመቱ በቱሪዝም ዘርፉ ለ30 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ 6 ሺህ 344 ቋሚ እና 11 ሺህ 327 ጊዜያዊ በአጠቃላይ ለ17 ሺህ 671 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉንም ተቁመዋል፡፡
አቶ አለማየሁ እንደገለጹት እንደ ገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ የቱሪዝም መሰረተ ልማቶች የመዘርጋት እና አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን የማልማት ሥራ በሥፋት መሠራቱ ለሀገር ውስጥ ብሎም ለውጭ ቱሪስቶች እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡
ይህም የሀገር ውስጥ ኾነ የውጭ ቱሪስቶች ያሉበትን አካባቢ ብቻ ሳይኾን በሀገሪቱ ተዘዋውረው የሚጎበኙአቸው መዳረሻዎች ታይተው የማያልቁ እና ሰፊ በመኾናቸው የቱሪስት መስህብ ከመኾናቸውም በላይ የቆይታ ጊዜን ለማራዘም የሚያስችሉ መኾናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
አቶ አለማየሁ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን ከማልማት እንዲሁም ነባሮችን ከማደስ እና ከመጠገን አንጻር ውጤታማ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በቀጣይም ዘርፉን ይበልጥ ለማነቃቃት በቱሪዝም እና በገበያ ልማት ላይ በትኩረት ይሠራል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደዘገበው የሃብት ውስንነት፣ የዱር እንስሳት አያያዝ፣ የቅርስ ምዝገባ እና ጥበቃ ላይ ያሉ የሕግ ክፍተቶች የዘርፉ ተግዳሮቶች መኾናቸውን ተጠቁሟል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!