“ወቅቱ ቁርጠኝነትን እና ፅናትን የሚጠይቅ ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

93

ባሕር ዳር፡ ኅዳር 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል የከፍተኛ እና የመከካለኛ መሪዎች በክልሉ ወቅተዊ ጉዳዮች እና በቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል። በባሕር ዳር የተካሄደውን ውይይት ላይ ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። በአማራ ክልል የተፈጠረው የሰላም እጦት ዜጎችን ለችግር ማጋለጡን ገልፀዋል። ክልሉ በኑሮ ውድነት፣ በሥራ እድል ፈጠራ እና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ችግር ያለበት መሆኑን አመላክተዋል። አሁን ያለው የክልሉ መሪ የተወሳሰበ እና ችግር በበዛበት ሁኔታ የሚመራ መሆኑንም አስታውቀዋል። ወቅቱ ቁርጠኝነትን እና ፅናትን የሚጠይቅ ነው ብለዋል። መስዋዕትነት የሚጠይቅ ወቅት ነው ብለዋል።

“የክልሉን ሕዝብ ችግር እፈታለሁ፣ የሚመጣውን ችግርም በጽናት እታገላለሁ” የሚል መሪ መኖሩንም ገልፀዋል። በአማራ ክልል በርካታ አካባቢዎች ወደ ሰላም መምጣታቸውን የገለጹት አቶ አረጋ፤ ሁሉም የዞን ማዕከላት ሰላም መሆናቸውን አስታውቀዋል። ክልሉ ቀደም ሲል ከነበረበት የጸጥታ ችግር እየወጣ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

አሁን እየተሠራ ባለው የሕግ ማስከበር ሥራ መቀጠል ከተቻለ ክልሉን በአጭር ጊዜ ውስጥ ነፃ ማድረግ ይቻላልም ብለዋል። ክልሉን የማናጋት እድል መክሸፉንም አስታውቀዋል። የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች በፓርቲም ሆነ በመንግሥት መፍታት እንደሚገባ መግባበት ላይ የተደረሰባቸው መሆናቸውንም ገልፀዋል። ችግሮችን ይዞ ከማራገብ ይልቅ መተንተን እና በጥልቀት መረዳት እንደሚገባም ተናግረዋል። ጥያቄዎችን ለማስመለስ ወደ ግጭት እና ፍጅት መግባት እንደማይገባም አሳስበዋል። በአማራ ክልል በተፈጠው የድርቅ ችግር ወገኖቻችን እንዳይሞቱ በከፍተኛ ትኩረት እየሠራን ነውም ብለዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገር ጠባቂ መሆኑን መረዳት እንደሚገባ አመላክተዋል። በሰሜኑ ጦርነት ባከበርነው እና በጠበቅነው ልክ አሁንም ማክበር ይገባል ነው ያሉት። መከላከያ ሠራዊት ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያውያን የቆመ መሆኑንም ገልፀዋል። መከላከያ ሠራዊትን የተለየ ስም መስጠት እና ማብጠልጠል የተገባ አለመሆኑንም አሳስበዋል።

ፋኖነት ለሀገር ነፃነት፣ ክብር እና ለሕዝብ አንድነት የቆመ መሆኑን ርእሰ መሥተዳድሩ ፋኖነት ብሔራዊ የጀግንነት ስም የሆነ፣ የኢትዮጵያን ነፃነት ያስከበረ መነሻውና መድረሻው የሀገርና የሕዝብ ክብር የሆነ መሆኑንም ገልፀዋል። ከፋኖ ልዕልና እና ማንነት መገለጫ ባፈነገጠ ያለው አካሄድ የተዛባ እና ትክክል አለመሆኑንም ተናግረዋል። የእኔን ሃሳብ ብቻ ካልተከተልክ እያለ የሚገድል የፋኖነት መገለጫ እና ማንነት አለመሆኑንም አስታውቀዋል።

የግጭት እና የጦርነት መቋጫው ሰላም ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ መንግሥት ተደጋጋሚ ውይይቶችን ማድረጉን እና ሰላማዊ አማራጮችን ማቅረቡንም ገልፀዋል። መንግሥት ሁልጊዜም ለውይይት ዝግጁ መሆኑንም አስታውቀዋል። የሕግ ማስከበር ሥራውን አጠናክሮ መቀጠል እና መደገፍ እንደሚገባም አሳስበዋል። ጠንካራ የፖለቲካ ሥራ መሥራት አስፈላጊው ጉዳይ መሆኑንም አመላክተዋል።

በፈተና ጊዜ በመፅናት ጀግና ሆኖ መውጣት እንደሚገባም አሳስበዋል። ወቅቱ ጀግና ሆኖ ለመውጣት እድል የሚሰጥ መሆኑንም አመላክተዋል። መሪዎች ሚናቸውን መለየት እና በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባቸውም ተናግረዋል። እውነትን ለሕዝብ እና ለመሪዎች መንገር እና መተግባር እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

የልማት ሥራዎችን በትኩረት እንዲሠሩም አስገንዝበዋል። የጤና አገልግሎት ላይ በትኩረት መሥራት ይገባልም ብለዋል። አገልግሎት አሰጣጥን ማስተካከል እንደሚገባ እና ሕዝብን በቅንነት ማገልግል ላይ ትኩረት እንዲደረግም አሳስበዋል። ሕገ ወጥ አሠራሮችን መታገል እንደሚገባም ገልፀዋል። የገቢ አሰበሰብ ሥራውን በትኩረት እንዲሠሩም አሳስበዋል። ክልሉ ከፍተኛ ወጪ እያወጣ መሆኑን የተናገሩት ርእሰ መሥተዳድሩ፤ ገቢን በሚገባ መሰብሰብ ካልተቻለ ሌላ ችግር እንደሚፈጠርም ገልፀዋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሥራ የክልሉ መንግሥት በትኩረት የሚሠራበት ጉዳይ መሆኑን የጠቆሙት ርእሰ መሥተዳድሩ፤ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ምቹ ሁኔታን መፍጠር እንደሚገባም አመላክተዋል። የማንነት እና የራስ አሥተዳደር ጥያቄ ሌላው በትኩረት እና በጥንቃቄ የሚሠራበት ጉዳይ መሆኑንም ገልፀዋል። ተፈናቃይ ወገኖችን ለመመለስ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በፖለቲካ ትግል ወዳጅን እያበዙ ጠላትን እየቀነሱ መሄድ አስፈላጊ መሆኑንም አሳስበዋል። ሁሉን አቀፍ እና የተቀናጀ ሥራ ላይ ትኩረት አንዲደረግም አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleተመላሽ የሠራዊት አባላት በዘላቂ ልማት የሚሰማሩበት አማራጭ እንዲመቻች ተጠየቀ።
Next articleከውጭ ጎብኝዎች አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ።