ተመላሽ የሠራዊት አባላት በዘላቂ ልማት የሚሰማሩበት አማራጭ እንዲመቻች ተጠየቀ።

36

ባሕር ዳር፡ ኅዳር 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ የሚገኙ ተመላሽ የሠራዊት አባላት በከተማ አሥተዳደሩ በተለያዩ የልማት ሥራዎች ተሠማርተዋል። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተመላሽ ሠራዊት ማኅበር ሰብሳቢ ሃምሳ አለቃ አስናቀው ይበልጣል እንዳሉት የተመላሽ ሠራዊት አባላት በከተማ አሥተዳደሩ በአክሲዮን በመደራጀት የጥበቃ ሥራ እየሠሩ ይገኛሉ።

ማኅበሩ ዛሬ በ 3 ሺህ 200 ካሬ ቦታ ላይ በ2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ወጭ የተሠራውን ሁለ ገብ መዝናኛ ቦታ ለአገልግሎት ክፍት አድርጓል። ሁለገብ መዝናኛ ቦታው የስብሰባ አዳራሽ፣ የሕጻናት መጫዎቻ፣ የመኪና ማቆሚያ፣ የዳቦ መጋገሪያ፣ ሱፐር ማርኬት እና የመሳሰሉ አገልግሎቶችን ያካተተ ነው። ማኅበሩ በቀጣይ ደግሞ በዘመናዊ የእንስሳት እርባታ እና ማድለብ ሥራ ላይ ለመሰማራት እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡ አባላቱ ከተማ አሥተዳደሩ መሠረተ ልማት እንዲያሟላላቸውም ጠይቀዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ የተመላሽ ሠራዊቱ አባላት በሀገር መከላከያ ሠራዊት ያገኙትን ሥልጠና እና ልምድ በልማት ላይ ለማዋል ለሚያደርጉት ሥራ ከተማ አሥተዳደሩ በሚችለው ሁሉ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል። ማንኛውንም ልማት ማከናወን የሚቻለው ሰላም ሲኖር በመኾኑ ምልስ የሠራዊት አባላት የአካባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅ የድርሻቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል። ወጣቱም ከምልስ ሠራዊቱ ግብረ ገብነትን እና ጽናትን ተምሮ ለሀገር አንድነት እና ለሰላም እንዲሠራ ጠይቀዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተመላሽ የመከላከያ ሠራዊት ማኅበር በ2013 ዓ.ም ነበር የተመሠረተው።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ለአብዛኞቹ ችግሮች መፍትሄ ያለው ከመሪዎች ነው፤ መሪዎችን ደግፎ መሥራት ያስፈልጋል” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)
Next article“ወቅቱ ቁርጠኝነትን እና ፅናትን የሚጠይቅ ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ