“ለአብዛኞቹ ችግሮች መፍትሄ ያለው ከመሪዎች ነው፤ መሪዎችን ደግፎ መሥራት ያስፈልጋል” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)

91

ባሕር ዳር፡ ኅዳር 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በተገኙበት የአማራ ክልል ከፍተኛ እና መካከለኛ መሪዎች በክልሉ ወቅታዊ ጉዳዮች እና በቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ውይይት አድርገዋል። በውይይቱ ላይ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) በመፍትሔዎች ለመግባባት ችግሮችን መረዳት እና በችግሮች ላይ የጋራ አቋም መያዝ ይገባል ብለዋል። አብዛኛው ችግር የመሪዎች ነው፣ መፍትሔውም ያለው ከመሪዎች ነው ብለዋል። መሪዎች ያለባቸውን ችግር ማረም እና ለመፍትሔው መሥራት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።

ለሕዝብ ጥቅም ቁርጠኛ እና ታማኝ መኾን ይገባልም ብለዋል። ለመሪዎች የተሰጠው ሥልጠናም ወደ ራስ ለመመልከት እንደሚያስችል ገልጸዋል። የነበረውን ችግር ጥሎ በቁርጠኝነት መሥራት ይገባል ነው ያሉት። እያዩ አለማየት፣ ሁለት ልብ መኾን እና ችግሮችን በቁርጠኝነት አለመፍታት መታረም አለበትም ብለዋል። መሪዎችን መደገፍ እና ተማምኖ መሥራት እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል። የጠራ እሳቤ መያዝ እና ከጎጠኝነት አስተሳሰብ መውጣት ካልተቻለ የክልሉን ችግር መፍታት እንደማይቻልም አመላክተዋል።

መሪዎች ስሁት ትርክቶችን ማረም፣ ሕዝባቸውን ማገልገል እና እውነታውን ማቅረብ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል። እውነት ላይ ቆመን እንታገል፣ የሚቀር ነገር ካለ ይቅርም ብለዋል። የአማራን ምጣኔ ሀብት እያወደሙ የአማራን ሕዝብ ጥያቄ መመለስ እንደማይቻልም አመላክተዋል። የአማራን ሕዝብ ጥያቄዎች ለመመለስ መላሾችን በመግደል እንደማይኾንም አሳስበዋል።

የትኛውንም የሕዝብ ጥያቄ በአንደነት መፍታት ይገባልም ብለዋል። የክልሉ መንግሥት መፍታት የሚገባውን ጥያቄዎች እየመለሰ መኾኑንም አመላክተዋል። ሕዝቡን በመያዝ እውነታውን በማስረዳት መመለስ ይገባልም ነው ያሉት። የከበረውን ስም ማስከበር እና መጠበቅ አስፈላጊ መኾኑንም አመላክተዋል። መሪዎች በድፍረት፣ በእውነት እና በፅናት ሕዝብን ማገልገል እንደሚገባቸውም አሳስበዋል። ለሚሠሩት ሥራ የክልሉ መንግሥት ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።

በክልሉ የግብርና ግብዓቶችን ለማሰራጨት እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። የትራንስፖርት ችግር እንዳይፈጠር መሥራት ይገባልም ብለዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ያገኙትን እውቀት ተጠቅመው የሕዝቡን ችግር እንዲፈቱ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) አሳስቡ።
Next articleተመላሽ የሠራዊት አባላት በዘላቂ ልማት የሚሰማሩበት አማራጭ እንዲመቻች ተጠየቀ።