የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ያገኙትን እውቀት ተጠቅመው የሕዝቡን ችግር እንዲፈቱ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) አሳስቡ።

44

ባሕር ዳር፡ ኅዳር 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሦስተኛውን ዙር የአመራር ሥልጠና አጠናቅቀው ለተመለሱ የደብረ ብርሃን ከተማ፣ ሰሜን ሸዋ ዞን እና ለኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎች የሥራ መመሪያ እየተሰጠ ይገኛል። በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ደረጃ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪና የአማራ ክልል ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) በመድረኩ ላይ ተገኝተው የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል።

ገዢ ሀገራዊ ትርክት እንዴት መገንባት እንችላለን የሚለው ጉዳይ የስልጠናው አካል እንደነበር አንስተዋል። በሥልጠናው የተገኘውን እውቀትና ልምድ የበለጠ ማዳበር፣ ያገኙትን ልምድ ለሚወክሉት ማኀበረሰብ ማስተላለፍን ጨምሮ ሕዝቡን አስተባብሮ ወደ ሥራ ሊያስገባ የሚችል የተግባር እቅድ ማዘጋጀት እንደሚስፈልግም ገልጸዋል።

በክልሉ ያጋጠሙ እንቅፋቶችንና ፈተናዎችን ለመፍታት መሥራት እንደሚጠበቅም አሳስበዋል።
ሰላምን የማስፈን ሥራው ቀዳሚ ተግባር ሊኾን ይገባል የሚል ሀሳብም አንስተዋል።
የሥነ ምግባር ብልሹነትን ለመታገልና ሥራ አጥነትን ለመቀነስም በትኩረት መሥራት ይገባል ነው ያሉት።

የደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብእሸት የአመራር አንድነትን በማጠናከር የክልሉን ችግር ለመፍታት ስልጠናዎች በዙር እየተሰጡ ነው ብለዋል።

ስልጠናው ተስፋ የተጣለበት በመኾኑ ለተግባራዊነቱ በጋራ መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ስልጠና የወሰዱ የሥራ ኀላፊዎች ለተግባራዊነቱ መረባረብ እና አጋዥ ተግባር መፈፀም ይገባቸዋል ተብሏል፡፡

ዘጋቢ፦ ደጀኔ በቀለ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“መስዋዕትነት ከፈለንም ቢኾን ክልሉን ሰላም ማድረግ አለብን” የክልሉ ከፍተኛ እና መካከለኛ መሪዎች
Next article“ለአብዛኞቹ ችግሮች መፍትሄ ያለው ከመሪዎች ነው፤ መሪዎችን ደግፎ መሥራት ያስፈልጋል” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)