
ባሕር ዳር: ኅዳር 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚመክር እና የቀጣይ አቅጣጫዎችን የሚያስቀምጥ የከፍተኛ እና መካከለኛ መሪዎች ውይይት እየተካሄደ ነው። መሪዎቹ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሥልጠና መውሰዳቸውን አመላክተው ሥልጠናዎቹ የአማራ ክልልን እውነታዎች ለማሳወቅ እና ለመተዋወቅ የሚያግዙ ነበሩ ብለዋል።
ሥልጠናው ለአማራ ክልል ይሰጠው የነበረውን የተዛባ አመለካከት ለማስተካከል እድል እንደሰጠም ተናግረዋል። በሥልጠናው ከመገናኘታችን አስቀድሞ ብዙ መራራቆች እና ልዩነቶች ነበሩብንም ብለዋል። የሕዝብ መፈናቀል እና መሳደድ የሁሉም ጥያቄ ነው ያሉት መሪዎቹ ለችግር መነሻ የኾኑ ጥያቄዎችን መመለስ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የክልሉ መንግሥት ከአዲስ አበባ ወደ አማራ ክልል ለመግባት እና ለመውጣት ነጻ እንቅስቃሴ እንዳይኖር ያደረገውን ችግር ከክልሎች እና ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመናበብ በዘላቂነት መፍታት ይገባልም ብለዋል። ወደ ዋና ከተማ እንዳይገባ የተደረገውን ሕዝብ ጥያቄ መመለስ፣ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመነጋገር የመንገድ ደኅንነት እንዲረጋጋጥ እና አስተማማኝ ጥበቃ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
የክልሉ መንግሥት በራሱ አቅም የሚፈታቸውን መፍታት፣ በፌዴራል መንግሥት የሚፈቱትን እንዲፈቱ ማስቻልም ይገባልም ብለዋል። በአንዳንድ አካባቢዎች የተጀመሩ የሰላም ለውጦችን ማጽናት እና በሁሉም ተደራሽ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት። የክልሉ መንግሥት የጸጥታ መዋቅር ማጠናከር እንደሚገባም ገልጸዋል። የክልሉን ችግር ሊፈታ የሚችለው የክልሉ መሪዎች ከሕዝብ ጋር ተቀናጅተው በመሥራት ነውም ብለዋል። በቁርጠኝነት እና በጽናት በመሥራት የክልሉን ሰላም ማረጋገጥ እንደሚገባም አመላክተዋል። መሪዎቹ መስዋዕት ከፍለንም ቢሆን ክልሉን ሰላም እናደርጋለን እንጂ በዚህ ወቅት መዘናጋት አይኖርብንም ነው ያሉት። በኢትዮጵያዊነት መንፈስ የምንተጋ መኾናችንን በተግባር ማሳየት ይገባናልም ብለዋል።
ከማስመሰል ወጥተን ለእውነት መታገል ይገባናል፣ መስዋዕት መሆን ካለብንም ሆነን ለእውነት እና ለሕዝብ ሰላም መሥራት አለብንም ብለዋል። በሥነ ምግባር በመቀረጽ እና በመከባበር መሥራት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። አሁንም የጸጥታ ችግር ያለባቸውን አካባቢዎች ማስተካከል እንደሚገባም አመላክተዋል። የገጠሩ አካባቢዎችን ሰላም ማጽናት እና አርሶ አደሮች የሚጠይቁትን ጥያቄ መመለስ በዘላቂነት ችግሮችን ይፈታልም ብለዋል።
ከላይ እስከ ታች ብርቱ ቅንጅት እና አንድነት በመፍጠር የሕዝብ ጥያቄዎችን መፍታት እንደሚገባም ገልጸዋል። የክልሉን መንግሥት መደገፍ እና ችግሮችን በጋራ መፍታት አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል። ጠንካራ እና ቁርጠኛ መሪዎችን ማፍራት የቀጣይ ትኩረት መሆን አለበትም ተብሏል። ሰላማዊ አማራጮችን መጠቀም እና የክልሉን ሰላም የሚረጋገጥበት መንገድ ማመቻቸት እንደሚገባም ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!