የአማራ ክልልን ወቅታዊ ጉዳዮች የሚዳስስ እና የቀጣይ አቅጣጫዎችን የሚያስቀምጥ ውይይት በአራት ማእከላት እየተካሄደ ነው።

42

ባሕር ዳር፡ ኅዳር 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ እና መካከለኛ መሪዎች ውይይት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በተገኙበት ባሕርዳርን ጨምሮ በአራት ማዕከላት እየተካሄደ መኾኑ ተመላክቷል። በአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ምክትል ኀላፊ ወይዘሮ ገበያ ተስፋ በአማራ ክልል በተፈጠረው የሰላም እጦት በርካታ አካባቢዎች በችግር ውስጥ መቆየታቸውን ገልጸዋል። የዜጎች እንቅስቃሴ መገደብ እና የልማት እንቅስቃሴዎች መስተጓጎል እንደገጠማቸውም አመላክተዋል።

በክልሉ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ፅናት እና ቁርጠኝነት የተላበሰ መሪ እና የፀጥታ ኀይል መፍጠር ይገባል ብለዋል። በሁሉም አካባቢዎች የሕግ የበላይነት ማረጋገጥ፣ የመልካም አሥተዳደር እና የልማት ሥራዎችን በሚገባ መምራት፣ የኮሙኒኬሽን ግንኙነቱን የተስተካከለ ማድረግ እና የውስጥ አንድነትን ማጠናከር ይገባል ነው ያሉት።

የፖለቲካ እና የአቅም ግንባታ ሥራዎችን በብቃት መፈፀም ይገባልም ብለዋል። እየመጡ ያሉ ለውጦችን በሁሉም አካበቢዎች ወጥ እና ፅኑ ማድረግ እንደሚገባ ተመላክቷል። አጀንዳ ተቀባይ ከመኾን በመውጣት በተረጋጋ መንፈስ ሥራን መከወን ይገባልም ብለዋል። በክልሉ ያለውን መሪ በአግባቡ ማደራጀት እና መምራት ይገባልም ተብሏል።

የመሪ እና የሕዝብ አንድነትን መፍጠር ወሳኙ ጉዳይ መኾኑንም ገልጸዋል። በሥራ እድል ፈጠራ፣ በኑሮ ውድነት እና በምርት ጭማሪ ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል።

ወቅቱን የሚመጥን የፖለቲካ ትንተና እንደሚጠበቅም ገልጸዋል። ለሕዝብ ሰላም እና አንድነት አደጋ የሚኾኑትን መታገል እና ማስተካከል እንደሚገባ አመላክተዋል። ከተለያዩ አደረጃጀቶች እና ማኅበሮች ጋር ስለ ሰላም እና አንድነት መምከር እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

ከላይ እስከታች ባሉ መሪዎች የማይፈፅሙትን ለሕዝብ ቃል አለመግባት እንደሚገባም አመላክተዋል። የክልሉን ሰላም በሚገባ ማረጋገጥ እና ወደተሟላ ሰላም መሄድ የቀጣይ ሥራ መኾኑንም ገልጸዋል። ለዘላቂ ሰላም ከሕዝብ ጋር አንድነት መፍጠር እንደሚገባም ተናግረዋል። ከመላው ሕዝብ ጋር ውይይት ማድረግ የቀጣይ ሥራ መኾን ይገባዋልም ብለዋል።

በአማራ ክልል የሚገኙ ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም እየተሠራ መኾኑም ተመላክቷል። የክልሉን መሠረታዊ ጥያቄዎች ለመፍታት በቁርጠኝነት እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። የሕዝብን ሥነ ልቡና ከፍ ማድረግ እና ከስጋት ማላቀቅ እንደሚገባም አመላክተዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleMaxxansa Gaazexaa Hirkoo: Sadaasa 15/2016
Next articleክልል አቀፍና ሀገር አቀፍ ፈተና ወስደው ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች የደብረ ብርሃን ትምህርት መምሪያ እውቅና ሰጠ።