4ኛው ዙር የመንግሥት አመራሮች ሥልጠና በባሕር ዳር ተጀምሯል።

88

ባሕር ዳር: ኅዳር 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ”ከዕዳ ወደ ምንዳ” በሚል መሪ ሀሳብ ከሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች የተሰባሰቡ የመንግሥት አመራሮች የሚሳተፉበት ሥልጠና በውቢቷና የጣና ፈርጧ ባሕር ዳር ከተማ ተጀምሯል።

በሥልጠናው የእንኳን ደህና መጣችሁ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ኢትዮጵያውያን በአንድ ላይ ስንኾን ድምጻችን ከፍ ብሎ ይሰማል፤ ውጤታማም እንኾናለን ብለዋል።

ኢትዮጵያዊነትንና አንድነትን ከፍ አድርገን መዘመር አለብን ብለዋል። ”ኢትዮጵያውያን አብረን ስንኾን ነው የሚያምርብን” ያሉት ከንቲባው የውጪ ጠላቶቻችን በሸረቡልን ሴራ መግባት እና በተሳሳተ ትርክት መመራት የለብንም ብለዋል።

እርስ በርስ የሚያጠራጥረንን ትርክት ጥለን የአንድነትን ገንብቶ የሚያሻግረውን የመከባበርና የመተሳሰብ ትርክት ይዘን ኢትዮጵያን ማሻገር ይገባል ነው ያሉት።

በአማራ ክልል ባለፉት ሦስት ወራት የጸጥታ ችግር ገጥሞ እንደነበር ያነሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ አሁን ላይ በመከላከያ ሠራዊት እና በሕዝቡ ጥረት ወደሰላም ተመልሰናል ብለዋል።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ባለፉት ሦስት ዙር ሥልጠናዎች አስደማሚ ፍቅርና መተሳሰብ በሠልጣኞች ዘንድ መታየቱን ጠቅሰው የሕዝቡን እንግዳ ተቀባይነት በቆይታችሁ የምታዩት ይኾናል ብለዋል።

ዘጋቢ:- ዋሴ ባየ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ተጠባቂው የማንቸስተር ሲቲ እና የሊቨርፑል ጨዋታ”
Next articleMaxxansa Gaazexaa Hirkoo: Sadaasa 15/2016