
ባሕር ዳር: ሕዳር 14 /2016 ዓ.ም (አሚኮ) የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግን ማንቸስተር ሲቲ በ28 ነጥብ እየመራው ይገኛል፡፡ ሊቨርፑል ደግሞ በ27 ነጥብ በሁለተኛነት ይከተላል፡፡ የፕሪሚየር ሊጉ የ13ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ቅዳሜ፣ እሁድ እና ሰኞ ይካሄዳሉ፡፡
ነገ ከሚካሄዱት ጨዋታዎች መካከል ቀን 9:30 ላይ ማንቸስተር ሲቲ 53 ሺህ 400 ተመልካቾች በሚይዘው የኢትሃድ ስታዲየም ሊቨርፑልን ይጋብዛል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች ካላቸው ወቅታዊ አቋም እና በአንድ ነጥብ ብቻ ደረጃቸው ከመለያየቱ አንጻር ጨዋታውን በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎታል፡፡
ማንቸስተር ሲቲ በዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ 12 ጨዋታዎችን አድርጎ በዘጠኙ ሲያሸንፍ በሁለቱ ደግሞ ተረትቷል፤ በአንድ ጨዋታ አቻ ወጥቷል፡፡ ሊቨርፑል በአንጻሩ 12 ጨዋታዎችን አድርጎ ስምንቱን በድል በመወጣት በአንዱ ብቻ ተሸንፎ በሦስት ጨዋታዎች አቻ ተለያያቷል፡፡
ሊቨርፑል እና ማንቸስተር ሲቲ በታሪክ በ224 ጨዋታዎች ተገናኝተዋል፡፡ ሊቨርፑል 108 ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ በ60 ተሸንፏል። በ56 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡
ማንቸስተር ሲቲ እና ሊቨርፑል ባለፉት 10 ዓመታት ውስጥ በፕሪሚየር ሊጉ ጠንካራ ክለቦች ኾነዋል።
በ51 ጨዋታዎች ተገናኝተውም ሊቨርፑል በ21 ጨዋታዎች አሸንፏል፡፡ ሲቲ ደግሞ በ11 ግጥሚያዎች ድል ነስቷል፡፡ በ19 ጨዋታዎች አቻ መለያየታቸውን ቢቢሲ ስፖርት በድረ ገጹ አስነብቧል፡፡
ሲቲ በአንፊልድ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ አንድ ጊዜ ብቻ ሲያሸንፍ ሊቨርፑል በተመሳሳይ በኢትሃድ በአምስት ጨዋታዎች አሸንፏል። የሁለቱ ክለቦች አሠልጣኞች ፔፕ ጋርዲዮላ እና የርገን ክሎፕ በሥራቸው ያሳለፉት ስኬታማ ጉዞ ሚዛን እንደሚያነሳ ስካይ ስፖርት አስነብቧል፡፡
የነገውን ጨዋታ አስመልክቶም የሊቨርፑል አሠልጣኝ የርገን ክሎፕ ” ጨዋታው ለእኛ እና ለእነሱ ወሳኝ ነው፤ የስፖርት ቤተሰቡ እና የመገናኛ አውታሮች በጉጉት የሚጠብቁትም ጨዋታ ነው ” በማለት ተናግሯል፡፡
የርገን አክሎም “በጨዋታው አሸንፈን የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ብቻ ለመኾን ሳይኾን ዋንጫ ለመውሰድ ነው የተዘጋጀነው ፡፡ በተለይ ደግሞ ጨዋታው በኢትሃድ እንደመደረጉ በደጋፊዎቻችን ሳይኾን በወዳጆቻን ፊት አሸንፈን ድሉን ጣፋጭ እንደምናድርግ ተስፋ አለኝ” ብሏል፡፡
አሰልጣኙ “እኔን የናፈቀኝ የማንቸስተር ሲቲ የልብ ደጋፊዎች ከመቀመጣቸው ተነስተው ጋርዲዮላ ደግሞ ተቀምጦ በአድናቆት ሲያጨበጭብልን መመልከት ነው” በማለት አስገራሚ አስተያየት ሰጥቷል፡፡
የቡድኑ አሰላለፍም 4-3-3 እንደሚኾን ፍንጭ ሰጥቷል፡፡ ሞሐመድ ሳላህ እና ሉዊስ ዲያዝ በመስመር ሲያጠቁ ዳርዊን ኑኔዝ ደግሞ ከፊት ኾኖ ያጠቃል ሲል አብራርቷል፡፡
የማንቸስተር ሲቲው አሠልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ በበኩላቸው ቀደም ሲል ኧርሊንግ ሃላንድ ቁርጭምጭሚቱ ላይ የደረሰበት ጉዳት አሳሳቢ ነው ከማለት ውጭ ደፍሮ ‘አይሰለፍም’ ማለትን አልደፈረም፡፡ “የርገን ክሎፕ አሸንፎ ሦስት ነጥብ ለመውሰድ እንደሚጫወት ይገባናል፤ እኛ ግን እንደ እነሱ 11 ተጫዋቾችን ሳይኾን የምናሰልፈው 12 ተጫዋቾችን ነው፤ ይህ የቁጥር ብልጫ ደግሞ ትልቅ አቅም ስለሚኾነን እናሸንፋለን” ብሏል፤ በሜዳቸው መጫዎታቸው ለውጤት እንደሚያግዛቸው ለመግለጽ።
የስፖርት ተንታኞች ይህን የጋርዲዮላ አገላለጽ ደጋፊዎቻቸውን ከወዲሁ ለማነቃቃት የተጠቀሙበት ጥበብ ነው ሲሉ አወድሰዋቸዋል፡፡ ጋርዲዮላ አክለውም የቡድናቸውን መነሻ አሰላለፍ 3-2-4-1 እንደሚኾን ጠቁመዋል፡፡ ስቴፋን ኦርቴጋ፣ ካይል ዎከር፣ ሩበን ዳያስ፣ ጆስኮ ግቫርድዮል፣ ሮድሪ፣ ማኑኤል አካንጂ፣ ፊል ፎደን፣ በርናርዶ ሲልቫ፣ ጃክ ግሬሊሽ፣ ጄረሚ ዶኩ፣ ጁልያን አልቫሬዝ…እያሉ ቀጠሉ ፤የሃላንድ ስም ግን አልጠቀሱም። በዘ ስፖርቲንግ ኒውስ ቅድመ ግምት መሰረት ጨዋታው በአቻ ውጤት ይጠናቀቃል፡፡
በሌሎች የፕሪሜር ሊጉ ጨዋታዎች ነገ ሉተን ከክሪስታል ፓላስ፣ኒውካስትል ከቼልሲ ፣ኖቲንግሃም ከ ብራይተን ፣በርንሌይከዌስት ሃም ፣ሸፊልድ ከበርንማውዝ ሁሉም ምሽት 12 ሰዓት ይጫወታሉ፡፡ የብሬንትፎርድ እና የአርሰናል ጨዋታ ምሽት 2 :30 ሰዓት ተኩል ላይ ይካሄዳል፡፡
በእሑድ መርሐ ግብር 11 ሰዓት ላይ ላይ ቶተንሃም ከአስቶን ቪላ፣ ምሽት 1 ሰዓት ተኩል ደግሞ ኤቨርተን ከማንቸስተር ዩናይትድ ይጫወታሉ፡፡
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!