
አዲስ አበባ: ኅዳር 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ)2ኛው የማዕድን እና የማዕድን ቴክኖሎጅ ኤክስፖ በሚሊኒየም አዳራሽ ተከፍቷል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እንደ ሀገር ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሀገር በቀል ማሻሻያው ትኩረት ከተሰጣቸው አምስት ዘርፎች የማዕድን ዘርፉ አንዱ ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ከውጭ የሚገባውን ማዕድን በሚያስቀር መልኩ ብቻ ሳይኾን ወደ ውጪ በመላክም ሀገርን ማልማት ይገባል” ብለዋል።
ኤክስፖው “የማዕድን ሀብታችን የነገ ተስፋችን” በሚል መሪ መልእክት ከሕዳር 14/2016 ዓ.ም እስከ ሕዳር 18/2016 ዓ.ም ለአምስት ተከታታይ ቀናት ለሕዝብ ክፍት ኾኖ እንደሚቆይም ተገልጿል፡፡
ከ2ኛው የማዕድን እና ቴክኖሎጅ ኤክስፖ ጎን ለጎን ውይይት የሚካሄድ ሲኾን የዘርፉ ልምድና ተሞክሮዎች ቀርበው በስፋት ውይይት ይደረግባቸዋልም ተብሏል፡፡
በኤክስፖው ላይ የማዕድን አምራቾች፣ ላኪዎች፣ የማዕድን ተጠቃሚዎች፣ የቴክኖሎጅ አምራችና አቅራቢዎች፣ ኢንቨስተሮች ፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ የሀገር ውስጥ እና የውጭ የዘርፉ ምሁራን እንደሚሳተፉም ነው የተብራራው።
በኤክስፖ መክፈቻው ላይ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ ሚኒስትሮች፣ የክልል ርእሳነ መሥተዳድሮች እና የተለያዩ ሀገራት ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡- ቤተልሄም ሰለሞን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!