
ባሕር ዳር: ሕዳር 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በ3 ወረዳዎች በ26 ቀበሌዎች በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ከ435 ሺህ በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎች አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ ያሥፈልጋቸዋል።
በመኾኑም የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የሚውል 302 ነጥብ 75 ኩንታል ፊኖ ዱቄት ድጋፍ አድርጓል።
ድጋፉን ያስረከቡት በአልማ የሰሜን ወሎ ዞን እና የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስተባባሪ ካሳሁን አንባየ አልማ ከአሁን ቀደምም ለተፈናቀሉ ወገኖች እና ለተቸገሩ ወገኖች ማኅበራዊ ኀላፊነቱን ለመዋጣት ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
በዛሬው ዕለትም በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ለሚገኙ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች 2 ሚሊዮን 738 ሺህ 544 ብር በማውጣት 302 ነጥብ 75 ኩንታል ፊኖ ዱቄት በምግብ ዋስትና በኩል እንዲደርሳቸው አስረክበናል ብለዋል።
አቶ ካሣሁን በክልሉ ባሉ 8 ዞኖች 19 ወረዳዎች እና 119 ቀበሌዎች በድርቅ የተጎዱ በመኾናቸው አስታውሰዋል፡፡ በቀጣይ አሥፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ አልማ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ሰብዓዊ ድጋፉን የተረከቡበት የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበርያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ምህረት መላኩ አልማ ከ302 ነጥብ 75 ኩንታል የፊኖ ዱቄት በማስረከቡ በማኅበረሰቡ ስም አመስግነዋል፡፡
ይህ ሰብዓዊ ድጋፍም ለ2 ሺህ 422 የማኅበረሰብ ክፍሎች የወር ቀለብ እንደሚኾን ገልጸዋል።
አቶ ምህረት ከዚህ ቀደም የፌዴራል እና የክልሉ መንግሥት ብሎም የወልድያ ዩኒቨርሰቲ፣ ወሎ ቤተ አምሐራ ለስሃላ ሰየምት ወረዳ ተጎጂ ማኅበረሰቦች እንደደገፉ ገልጸዋል፡፡
ለቀጣይም ችግሩ አንገብጋቢ እና አፋጣኝ ድጋፍ የሚጠይቅ በመኾኑ መንግሥታዊ ድርጅቶች፣ ረጅ ድርጅቶች፣ የፌዴራል መንግሥት እና በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የተለመደ ትብብራቸውን እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!