
ባሕር ዳር: ሕዳር 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወደ ተግባር የገባው ዘመናዊ የመሬት አያያዝ ሥርዓት ግብርን ከማሳደግ እና ከመሬት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን በመፍታት በኩል ጠቅሜታው የጎላ ሆኗል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር የብድር ተጠቃሚ በመኾናቸው ገቢያቸውን ማሳደግ መቻላቸውን ያነጋገርናቸው አርሶ አደር ነግረውናል፡፡
ከተጠቃሚዎች ውስጥ በደቡብ ጎንደር ዞን ቆራጣ ቀበሌ ነዋሪ የኔአንተ ጋሻው አንዱ ናቸው፡፡ በ2015 ዓ.ም በሁለተኛ ደረጃ አረንጓዴ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ከጸደይ ባንክ 50 ሺህ ብር በመበደር የምርት ማሳደጊያ ግብዓት ተጠቅመዋል፡፡
በዚህም ከፍተኛ ምርት እንዳገኙ ነው የገለጹት፡፡ አሁን ላይ ደግሞ ወደ ሦስት እግር ተሸከርካሪ ማሳደግ ችለዋል፡፡ ‹‹ዘመናዊ የመሬት አያያዝ ሥርዓቱ ግጭቶችን ከመቅረፍ ባሻገር የገቢ አቅማችንን ለማሳደግ ጠቅሞናል›› ብለዋል አርሶ አደር የኔአንተ፡፡
አሁን ላይ ያወጡትን ብድር በአብዛኛው መመለስ ችለዋል፡፡ ከዚህ በፊት ግብዓት በወቅቱ ለማቅረብ ይቸገሩ እንደነበር ያነሱት አርሶ አደር የኔአንተ የይዞታ ማረጋገጫ ተጠቃሚ ከኾኑ ጀምሮ ችግሩ መፈታቱን ገልጸዋል፡፡ በቀጣይም ተጨማሪ ብድር ተጠቃሚ በመኾን በተለያዩ የልማት ሥራዎች ለመሰማራት ማቀዳቸውን ነው የተናገሩት፡፡
የአማራ ክልል መሬት ቢሮ የገጠር መሬት አሥተዳደር እና ካዳስተር ዳይሬክተር ታከለ ሀብቴ እንዳሉት በአማራ ክልል የካዳስተር ሥራ በተሠራባቸው 12 ዞኖች 11 የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ለአርሶ አደሮች ብድር እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡ እስከ 2015 በጀት ዓመት መጨረሻ 12 ሺህ 668 ባለይዞታ አርሶ አደሮች የብድር ተጠቃሚ ኾነዋል፡፡
ከ728 ሚሊዮን 971 ሺህ ብር በላይ ብድር ደግሞ ተሰራጭቷል ብለዋል፡፡ የብድር አቅርቦት አርሶ አደሮች ምርት እና ምርታማነትን ሊያሻሽሉ የሚችሉ ግብዓቶችን በወቅቱ እንዲያገኙ እና በወቅቱ የሰብል ልማት ሥራ እንዲሠሩ አድርጓቸዋል፡፡
ከሰብል ልማት ባለፈ በእንስሳት እርባታ፣ በመስኖ ልማት፣ በንግድ እና በመሳሰሉ አማራጭ የልማት ሥራዎች ላይ በመሰማራት ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ እድል መፍጠሩን አንስተዋል፡፡ ከተሰራጨው ብድር 98 በመቶ መመለሱንም ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡
በ2016 በጀት ዓመትም አርሶ አደሮችን በስፋት የብድር ተጠቃሚ ለማድረግ ቢታቀድም በክልሉ በተፈጠረው ችግር ምክንያት የተሠራጨውን ብድር ማወቅ አለመቻሉን ነው የገለጹት፡፡
የብድር አቅርቦቱ በክልሉ ካለው 2 ሚሊዮን 660 ሺህ የሁለተኛ ደረጃ አረንጓዴ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ተጠቃሚ አርሶ አደሮች አንጻር ዝቅተኛ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ የብድር አቅራቢ ተቋማት ዘመናዊ የመሬት አያያዝ ሥርዓት በተጀመረባቸው 117 ወረዳዎች በተደራጀ መንገድ እንዲሠሩ ማድረግ የቀጣይ አቅጣጫ መኾኑንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!