
ባሕር ዳር: ሕዳር 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ወሎ ዞን በፍራፍሬ ምርት የተሰማሩ አርሶ አደሮች ከ3 መቶ 35 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ሰብስበው ለገበያ በማቅረብ ከምርት ሽያጭ ተጠቃሚ መኾናቸውን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል።
በሐብሩ ወረዳ የቡሆሮ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አራጋው አስፋው እንዳሉት በጓሯቸው በግማሽ ሔክታር መሬት ላይ ያለሙትን ፓፓያ እና አቦካዶ ለገበያ በማቅረብ 175 ሺህ ብር ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
የፍራፍሬ ልማት በገቢ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ጠቅሰዋል፡፡ በቀጣይ የተሻሻሉ ዝርያዎችን በመጠቀም ልማቱን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
የፍራፍሬ ልማቱ ለልጆቻችን የሥራ ምንጭ ኾኗል ያሉት ደግሞ በራያ ቆቦ ወረዳ 07 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሞላ ደስዬ ናቸው።
እንደ አርሶ አደሮቹ ገለጻ ከግማሽ ሔክታር በሚበልጥ መሬት በክረምት በዝናብ እና በበጋ በመስኖ ፓፓያ እና ማንጎ እያለሙ መኾናቸውን ገልጸዋል።
በተለያየ ጊዜ አምርተው ለገበያ ባቀረቡት የምርት ሽያጭም ከ270 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
በመምሪያው የአትክልት እና ፍራፍሬ ባለሙያ ወርቁ መለሰ የአርሶ አደሮች ኑሮ ለማሻሻል ከሰብል ምርቱ በተጓዳኝ በፍራፍሬ ምርት ተሰማርቶ ውጤታማ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡
የፍራፍሬ ምርቱ የተሰበሰበው በ853 ሄክታር መሬት በቆላ እና ደጋ ፍራፍሬ ከለማው መሬት ሲኾን በዚሁ ልማትም ከ42 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች መሳተፋቸውን ገልጸዋል።
በአርሶ አደሮቹ ከለሙት ፍራፍሬዎች መካከልም ፓፓያ፣ ሙዝ፣ ማንጎ፣ አቡካዶ ብርቱካን እና አፕል እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል፡፡ ከምርት ሽያጭ ከ217 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘት እንደቻሉ ተናግረዋል።
ምርቱ ተመርቶ ለገበያ የቀረበውም ከሰኔ ወር 2015 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 2016 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ እንደኾነ አመልክተዋል፡፡ የልማት ሥራው በዚህ የበጋ ወቅትም በመስኖ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው በዞኑ ባለፈው ዓመት አርሶ አደሮቹ ከፍራፍሬ ምርት ሽያጭ ከ215 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘት እንደቻሉ ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!