በጦርነት ብዙ መከራ አሳልፈናል፤ ሰላም እንፈልጋለን ሲሉ በደቡብ ወሎ ዞን የቱሉ አውሊያ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

49

ባሕር ዳር: ኅዳር 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የከተማዋና በዙሪያዋ የሚገኙ የገጠር ቀበሌ ነዋሪዎች በወቅታዊ የፀጥታና የሰላም ጉዳዮች ዙሪያ ከፖለቲካና ከፀጥታ አመራሩ ጋር እየመከሩ ነው፡፡

በከተማው ሰላም ቢኖርም በአጎራባች ወረዳዎች እየተፈፀመ ያለው ሕገወጥነት እንዳሳሰባቸው ነው የውይይቱ ተሳታፊዎች የተናገሩት፡፡

አርሶ አደሩ፣ የከተማው ነዋሪዎች እና ነጋዴው እንደፈለገ ተንቀሳቅሶ ለመሥራት እና ኑሮውን ለመግፋት በእጅጉ እየተፈተነ ነው ብለዋል ተሳታፊዎቹ፡፡

በፀጥታ እና የፖለቲካ አመራሮች ላይ የሚደርሰው ማስፈራራት በአካባቢው ያለውን ሕገወጥነት መበራከት ያሳያል ያሉት ተወያዮቹ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ መንግሥት ሕዝቡን አስተባብሮ ይሥራ ብለዋል፡፡

እንደልብ ምርትና ሸቀጥ ከቦታ ቦታ ባለመንቀሳቀሱ የኑሮ ውድነቱ ተባብሶ መቀጠሉም ተገልጿል፡፡ መንግሥት የሚያስተላልፈውን የሰላም ጥሪ የታጠቁ ኃይሎች ተቀብለው በውይይት ችግሮችን ልንፈታ ይገባልም ነው ያሉት፡፡

ሀገርን ከብዙ መከራ እየታደገ ያለውን ሠራዊት ስሙን በማጥፋት የሚደረግበትን ዘመቻ በጽኑ እንደሚያወግዙም የከተማ አሥተዳደሩ ነዋሪዎች አስረድተዋል፡፡

ውይይቱን የመሩት የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን ክልሉ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ኾኖ በተሠራው ሕግን የማስከበር ሥራ ለውጦች መመዝገባቸውን አንስተዋል፡፡

ይሁን እንጅ አሁን ላይም በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ከሕግ እና ሥርዓት ያፈነገጡ ተግባራት እየተከናወኑ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡

ኅብረተሰቡ ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ በማቅረብ መፍትሄ እንደሚገኝ አውቆ በታጠቁ ቡድኖች የተሳሳተ ጥሪ እንዳይደናገር አሳስበዋል፡፡

ሕግ እና ሥርዓትን በአፈሙዝ ለመናድ የተደረጉ ሙከራዎች ሁሉ አዋጭ አለመኾናቸውን ከሰሜኑ ጦርነት መማር ይገባልም ብለዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን እና የደሴ ከተማ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ብርጋዴል ጀኔራል ዘውዱ ሰጣርጌ የሠራዊቱን ክብር እና ዝና በማድረግ ከኢትዮጵያዊነት ከፍታ ሊያወርዱት የሚዳዳቸው አካላት እስካሁንም አልተሳካላቸውም ወደፊትም አይሳካላቸውም ብለዋል፡፡

ብርጋዴል ጀኔራል ዘውዱ ከሁሉም በላይ ግን ልዩነቶችን በንግግር ለመፍታት አማራጮችን ሁሉ መጠቀም ለነገ የማይባል ሥራ መኾን ይኖርበታል ነው ያሉት፡፡ ለዚህ ተግባር ደግሞ ኅብረተሰቡ የማይተካ ሚና እንዳለውም አስገንዝበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ጀማል ይማም

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article”የቦረና ሳይንት ወረሂመኑ ብሔራዊ ፓርክን ከአደጋ መጠበቅ እንደሚያስፈልግ የአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ገለጸ።
Next articleበሰሜን ወሎ ዞን ከፍራፍሬ ልማት ከ3 መቶ 35 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ተገኝቷል።