”የቦረና ሳይንት ወረሂመኑ ብሔራዊ ፓርክን ከአደጋ መጠበቅ እንደሚያስፈልግ የአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ገለጸ።

26

ባሕር ዳር: ኅዳር 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ቦረና ሳይንት ወረሂመኑ ብሔራዊ ፓርክ በወቅታዊ የሰላም መደፍረስ ምክንያት አደጋ እየተጋረጠበት መኾኑን የፓርኩ ጥበቃ ክፍል ኀላፊ አንተነህ ተስፋየ አስታውቀዋል። በአካባቢው በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የጥበቃ ሠራተኞች ሥራቸውን ተረጋግተው መሥራት አለመቻላቸውን እና ፓርኩን ከሚያዋስኑት ወረዳዎች መካከልም በመሃል ሳይንት፣ በቦረና፣ በለጋምቦ ወረዳዎች በግጦሽ፣ በእርሻ እና በምንጠራ አደጋ የተጋረጠበት መኾኑን ነው ኀላፊው የገለጹት።

በአንጻሩ ይህ ዘገባ እስከተሠራበት ጊዜ ድረስ በመቅደላ እና ተንታ ወረዳዎች እንዲኹም በመሃል ሳይንት ውስን ቀበሌዎች ፓርኩ አለመደፈሩን አቶ አንተነህ ገልጸዋል።
የመሃል ሳይንት ወረዳ የ036 ቀበሌ ነዋሪ በቀለ በላይ በአካባቢያቸው የሚገኘውን የፓርኩን ክፍል በቤተክርስቲያን ሰበካ ጉባዔ እና በአካባቢ እድር አማካይነት ከኅብረተሰቡ ጋር በመወያየት ፓርኩ እንዳይደፈር ተስማምተው እየጠበቁት መኾኑን ተናግረዋል።

በወቅታዊ ሁኔታዎች የአካባቢው የሰላም መደፍረስ ሲጀምር ከፓርኩ ውስጥ እንጨት ማውጣት ተጀምሮ እንደነበር የጠቀሱት አቶ በቀለ በችግር ጊዜ ለከብቶቻችን ሣር የምናገኝበትን ፓርክ ማውደም እንደሌለብን ተማምነን ነው ያስቆምነው ብለዋል። በዕድር ዳኞች እና በቤተ ክርስቲያን አባቶች አማካኝነት ተሰባስበን መስቀል ወጥቶ ”ፓርኩን የሚያጠፋ ሰው ቢገኝ ሕግ ይሙት! መንግሥት ይሙት!ዕድር(ቅሬ) ሰባት ዓመት ይዘጋ ብለን ቃል ገብተናል” ነው ያሉት። በዚህ ቃል ተማምሎ የተስማማ ሰው ለማፍረስ አይሞክርም፤ የአካባቢው ባሕላዊ ክቡር መሃላ ነው ብለዋል።

በፓርኩ ጥናት እና ምርምር ያደረጉት በወሎ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ምድር መምህር አሞኘ አስፋው (ዶ.ር) ፓርኩን በዘላቂነት ስለሚጠበቅበት አማራጭ ለሁለተኛ ዲግሪ ማሟያ ጥናት ማድረጋቸውን ጠቅሰው ፓርኩ ለሥነ ምኅዳር እና ለቱሪዝም ከፍተኛ አቅም ያለው መኾኑን ገልጸዋል።

ዶክተር አሞኘ በወቅታዊ የፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት በፓርኩ ላይ አደጋ ማንዣበቡ ከዚህ በፊትም የተከሰተ መኾኑን አስታውሰዋል፡፡ መፍትሔ ሲጠቁሙም ለፓርኩ መሰረተ ልማት ማሟላት፣ የቱሪስት መዳረሻ ማድረግ፣ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ማድረግ እና በችግር ጊዜ በባለቤትነት ስሜት እንዲጠብቀው ማድረግ ነው ብለዋል። አማራጭ የገቢ ምንጭም ለአካባቢው ነዋሪዎች ማመቻቸት አሥፈላጊ መኾኑን ጠቅሰዋል።

ዶክተር አሞኘ መፍትሔ እስኪገኝለት ድረስ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና እድሮች ፓርኩን ጠብቆ የማቆየት ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

በአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን የዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክተር አበባው አባይነህ በፓርኩ አካባቢ ልቅ ግጦሽ፣ የዱር እንስሳትን ማደን እና እርሻ መጀመሩን መረጃ እንዳገኙ ገልጸዋል። ከዚህ ቀደም ለማኅበረሰቡ ስለ ፓርኩ ጠቀሜታ የግንዛቤ ሥራ መሰራቱን የጠቀሱት አቶ አበባው የተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ጥፋት ሊፈጽሙ ይችላሉ ብለዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎችና ተወላጅ ምሁራን፣ የተፈጥሮ ሃብት ጉዳይ የሚያሳስባቸው አካላት፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች እና በአካባቢው የሚገኙ ኃይሎችም ፓርኩ ሲወድም እያዩ ዝም እንዳይሉ ነው አቶ አበባው የጠየቁት።

”ትውልድ አልፎ ትውልድ ቢተካ፤ ፖለቲካም ቢለዋወጥ ፓርኩ ከአባቶቻችን አግኝተን ለልጅ ልጅ የምናስተላልፈው ስለኾነ ለአካባቢው እና ለሀገር ተቆርቋሪ የኾነ ሁሉ ፓርኩ ሲወድም በቸለልተኝነት ማየት የለበትም” ሲሉ አሳስበዋል።

ዘጋቢ:- ዋሴ ባየ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article952 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ እና 320 ሚሊዮን ብር ከብክነት ማዳኑን የአማራ ክልል ሥነ-ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ገለጸ።
Next articleበጦርነት ብዙ መከራ አሳልፈናል፤ ሰላም እንፈልጋለን ሲሉ በደቡብ ወሎ ዞን የቱሉ አውሊያ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡