
ባሕር ዳር: ኅዳር 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የዓለም ፀረ ሙስና ቀን በአማራ ክልል በተለያዩ ኹነቶች እየተከበረ ነው። በኢትዮጵያ ለ19ኛ ጊዜ የሚከበረውን የዓለም የፀረ ሙስና ቀንን ምክንያት በማድረግ የአማራ ክልል ሥነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መግለጫ ሠጥቷል።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ሐብታሙ ሞገስ የዘንድሮው በዓል ከኅዳር 5/2016 ዓ.ም እስከ ኅዳር 30/2016 ዓ.ም በተለያዩ ኹነቶች እየተከበረ መኾኑን ገልጸዋል።
በአማራ ክልል ሙስናን ለመከላከል የተለያዩ ሥራዎች መሠራታቸውን የጠቀሱት ኮሚሽነሩ አሁንም ግን የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር እንቅፋት መኾኑ እንደቀጠለ መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡
በአማራ ክልልም በሰሜኑ ጦርነት እና በወቅታዊ የጸጥታ ችግሩ ምክንያት ሙስና እና ብልሹ አሠራር በብዙ አካባቢዎች እንዲጠናከሩ አድርጓል።
ኮሚሽነር ሐብታሙ በክልሉ የሙስና ቀን ሲከበር የተቋረጡ አገልግሎቶችን በማስቀጠል፣ የፓናል ውይይት እና የሃብት ምዝገባ በማድረግ እንዲሁም በትምህርት ቤቶች የሥነ ምግባር ግንባታ ይሠራል ብለዋል።
ሰዎችን ከስሶ በማስቀጣት በኩል ከቀረቡ 700 ጥቆማዎች ውስጥ 380 ለምርመራ ተልከዋል፡፡ 117 ተጣርተው ለፍትሕ መላካቸውን ኮሚሽነር ሐብታሙ ጠቅሰዋል። በዚህም 203 ሺህ ካሬ የከተማ ቦታ፣ 13 የመኖሪያ ቤት እና 5 ተሽከርካሪ መታገዱን ኮሚሽነር ሐብታሙ ገልጸዋል።
በክልሉ 952 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ እና 320 ሚሊዮን ብር ከብክነት ማዳን መቻሉንም ነው ኮሚሽነሩ የተናገሩት። በጨረታ አላግባብ ሊከፈል የነበረ 50 ሚሊዮን ብር እና የሊዝ ውልን አሳስቶ በመመዝገብ መንግሥት ሊያጣው የነበረ 270 ሚሊዮን ብር ኮሚሽኑ ማዳኑንም ነው ኮሚሽነሩ የገለጹት። በ36 መዝገብ 56 ተከሳሾች መኖራቸውንም አክለው ጠቅሰዋል።
ያም ኾኖ ”የሙስናን ጉዳት እየጨመረ በመኾኑ በአንድነት መታገልም የወቅቱ የህልውና ጉዳይ ነው” ያሉት ኮሚሽነሩ የሙስና ቀንን ስናከብር ሙስናን መታገል የወቅቱ ወሳኝ ጉዳይ ነው ብለዋል።
ኅብረተሰቡ በማሥረጃ የተደገፈ ጥቆማ በማድረግም ለፀረ ሙስና ትግሉ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!