
ባሕር ዳር: ኅዳር 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 4ኛውን ዙር የአመራሮች ሥልጠና ለመሳተፍ ወደ ባሕር ዳር ከተማ የገቡ እንግዶች ከደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ጀምሮ በክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች እና በባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ እንግዶችን “እንኳን ደህና መጣችሁ” በማለት ተቀብለዋል። እንግዶች በባሕር ዳር ከተማ በሚኖራቸው ቆይታ ለሥልጠናቸው መሳካት የሚያስፈልገው ድጋፍ ሁሉ ይደረጋል ብለዋል።
የአማራ ክልል ዴሞክራሲ ባሕል ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ግርማ መለሠ (ዶ.ር) ወደ አማራ ክልል የመጡ የመንግሥት አመራሮች የተሳካ የሥልጠና ጊዜ እንዲኖራቸው አስፈላጊው ሁሉ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
ወደ ባሕር ዳር ከተማ የገባችሁ የዚህ ዙር ሠልጣኞች እንግዳ ወዳድ ወደኾነ ሕዝብ ነው የመጣችሁ፤ ቆይታችሁ ያማረ ይኾናል ሲሉም ተናግረዋል።
ዶክተር ግርማ “አማራ ክልል ሀገር ወዳድ እና ከኢትዮጵያዊነት ደረጃው ዝቅ የማይል ሕዝብ ባለቤት ነው” ሲሉም ተናግረዋል። ይህ ሕዝብ ወደ አላስፈላጊ ግጭት እንዲገባ ቢደረግም ችግሮችን በሆደ ሰፊነት እያለፈ ሰላሙን እያረጋገጠ ይገኛል ብለዋል።
የአማራ ክልል ሕዝብ ጥያቄዎች በንግግር እና በሃሳብ ልዕልና እንደሚፈቱ ጠንቅቆ የሚረዳ፣ በአፈሙዝ የማያምን እና ሰላም ወዳድ ነው ሲሉም ዶክተር ግርማ ተናግረዋል።
ሠልጣኞች በክልሉ በሚኖራቸው ቆይታ የሕዝቡን እውነተኛ ሀገር ወዳድነት፣ ሰው አክባሪነት እና በሀገራዊ አንድነት አማኝ መኾኑን የመመልከት እድል እንደሚኖራቸውም ዶክተር ግርማ ገልጸዋል።
ሥልጠናው የኢትዮጵያን ሕዝብ ለማገልገል ዕውቀት እና ክሕሎት ከማስጨበጥ በተጨማሪ እርስ በእርስ ለመተዋወቅ መልካም አጋጣሚ እንደሚኾንም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!