“ኢትዮጵያ በዕርዳታ ስንዴ የሚሰፈርላት ሀገር መባል አይመጥናትም”የግብርና ሚኒስቴር

58

ባሕር ዳር: ኅዳር 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እስካሁን ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን ግብርና ሚኒስቴር ገልጿል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ.ር) ኢትዮጵያ ለስንዴ ምርት በጣም አመቺ መኾኗን አውስተዋል። በዓመት በሦስት ዙር የስንዴ ልማት በማካሄድ ውጤታማ ለማድረግ እየተሠራ ይገኛልም ነው ያሉት፡፡ እስካሁንም በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን ተናግረዋል፡፡

በዘንድሮ ዓመት የስንዴን ምርት እና ምርታማነትን ለመጨመር በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።በያዝነው ዓመት በበጋ መስኖ ልማት ብቻ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በስንዴ ሰብል በመሸፈን 147 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱንም ነው ዶክተር መለስ የተናገሩት ፡፡

እስካሁን ድረስም ቀድመው መዘራት በሚገባቸው አካባቢዎች ርብርብ በማድረግ ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ በስንዴ ዘር መሸፈን መቻሉን ጠቁመዋል። ምርት እየተሰበሰበ በሚገኙባቸው አካባቢዎችም ወዲያው ወደ እርሻ ሥራ እንዲገባ እየተደረገ በመኾኑ እቅዱ ይሳካል ብለዋል።

ሀገሪቱ ስንዴን ከውጭ ለማስገባት በዓመት ከአንድ ቢሊዮን ያላነሰ የአሜሪካ ዶላር እንደምታወጣ ያወሱት መለስ መኮንን (ዶ.ር)፤ ባለፉት ዓመታት ስንዴ ልማቱ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ በመሠራቱ ይህንን ወጪ ለማስቀረት እንደተቻለም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የማልማት አቅም እያላት በዕርዳታ ስንዴ የሚሰፈርላት ሀገር መባል አይመጥናትም ብለዋል። ይህ የስንዴ ልማት የሀገር ውስጥ ፍጆታዋን በራሷ ከማሟላት ባሻገር ለውጭ ገበያም ለማቅረብ የሚያስችላት ነው ሲሉ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

የስንዴ ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት በርካታ ፈተናዎች እንደሚኖሩም አንስተዋል ሚኒስትር ዴኤታው። ዘመናዊ አሠራሮችን ከመጠቀም ጀምሮ በተባይ እና በበሽታ የሚመጣው ጉዳት ትልቅ ፈተና መኾኑን አስገንዝበዋል።

ኢፕድ እንደዘገበው በስንዴ ላይ ብዙ ጊዜ የሚስተዋሉት በሽታዎች ዋግ እና ፉዛሪየምን መኾናቸውንም አንስተዋል።

በሽታዎቹን ለመከላከልም ባለሙያዎችን የማሠልጠን እና አቀናጅቶ መስክ የማሠማራት ሥራ እየተሠራ ይገኛል። ለዋግም ለፉዛሪየም በሽታዎች የሚኾኑ ኬሚካሎችን በየጊዜው ለአርሶ አደሩ በማቅረብ ችግሩ እንዳይከሰት በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ወደ ባሕር ዳር እየገቡ ነው።
Next article“አማራ ክልል ሀገር ወዳድ እና ከኢትዮጵያዊነት ደረጃው ዝቅ የማይል ሕዝብ ባለቤት ነው” ግርማ መለሠ (ዶ.ር)