
ባሕር ዳር: ኅዳር 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከኢትዮጵያ አራቱም ማዕዘን የተሰባሰቡ የመንግሥት አመራሮች 4ኛውን ዙር የአቅም ግንባታ ሥልጠና ለመካፈል ወደ ውቢቷ ባሕር ዳር ከተማ እየገቡ ነው። የጣና ፈርጧ ባሕር ዳርም በሰፊው ተሰናዳታ እንግዶቿን እየተቀበለች ነው።
የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች እና የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች በደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተገኝተው እንግዶቻቸውን እየተቀበሉ ነው።
ወደ ከተማዋ የገቡ እንግዶችን “የኢትዮጵያን መልክ የወከላችሁ እናንተ የኢትዮጵያ ልጆች ኾይ፣ ኢትዮጵያን ወዳድ ወደኾኑት የአማራ ክልል ወገኖቻችሁ መጥታችኃልና ቤታችን ቤታችሁ ነው” ብለው ተቀብለዋቸዋል እንግዳ ወዳድ የባሕር ዳር ነዋሪዎች።
የእንግዶች ቆይታ ያማረ እንዲኾንላቸው መልካም ምኞታቸውን ገልጸው ከሥልጠናቸው ጎን ለጎን በከተማው እና በአካባቢው ተዘዋውረው የሕዝቡን አኗኗር፣ ባሕሉን፣ ወጉን፣ እሴቱን እና የልማቱን ደረጃ እንዲመለከቱም ነዋሪዎች በክብር ጋብዘዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!