“የቆምነው ለሠንደቅ ዓላማ እና ለኢትዮጵያ ነው” ሌትናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ

90

ባሕር ዳር: ኅዳር 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና ጄኔራል መኮንኖች በተገኙበት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ተደርጓል።

በውይይቱ የተገኙት የሰሜን ምዕራብ እዝ አዛዥ ሌትናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ ሕዝብ ብቻ ሳይኾን መከላከያውም ሰላም እንዲኖር ይፈልጋል ነው ያሉት።

የሀገር መከላከያ ሠረዊት የሚዋጋው ለሀገር ሉዓላዊነት እና ለሕዝበ ሰላም መኾኑንም ተናግረዋል። የሕዝብ ጥያቄዎች እንዲመለሱ ሰላም እንዲመጣ ሁሉም ስለ ሰላም መሥራት እንደሚገባውም ተናግረዋል።

እኛ የእናንተ የኢትዮጵያ ሠራዊት ነንም ብለዋል። የኢትዮጵያ ሠራዊት ደግሞ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ተንቀሳቅሶ ለሕዝብ ሰላም ይሠራል ነው ያሉት። የሀገር መከላከያ ሠራዊት ለሕዝብ ሰላም እና አንድነት ሲባል ይሞታልም ብለዋል።
ሕዝቡ ለሰላም እንዲሠራም አሳስበዋል።

የራስ ሃሳብን ብቻ የሚያራምድ እና ሌሎችን የማይቀበል አካሄድ ሀገር የሚያፈርስ መኾኑንም ገልጸዋል። ለማንም ሳናዳላ፣ ለሀገር ሉዓላዊነት እና ለሕዝብ ሰላም እንሰራለንም ብለዋል። በሰላማዊ መንገድ የመጣውን እንቀበላለን ነው ያሉት። እኛ የሀገር ሉዓላዊነት ጠባቂዎች ነንም ብለዋል።

“የቆምነው ለሠንደቅ ዓላማ እና ለኢትዮጵያ ነው” ያሉት ሌተናል ጄኔራሉ እውነትን እያወጡ ለሀገር ሰላም መቆም እንደሚገባም አመላክተዋል። በሰላማዊ መንግድ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባም አመላክተዋል።

ሰከን ብሎ በማሰብ ክልሉን ወደ ሰላም መመለስ ይገባል ያሉት ደግሞ የሰሜን ምዕራብ እዝ ምክትል አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ሙሉዓለም አድማሱ ናቸው
ሜጄር ጀኔራል ሙሉዓለም ሰራዊቱ ለአማራ ሕዝብ ታላቅ ክብር አለው ብለዋል። በሰሜኑ ጦርነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገ ሕዝብ ነው ያሉት ሜጀር ጄኔራል ሙሉዓለም በአልተገባ መንገድ ሕዝብ ማወናበድ ሕዝብን ለመከራ እንደሚዳርግ አመላክተዋል።

የሕዝብን መከራ ለማቃለል እውነትን መሠረት በማድረግ መነጋገር ይገባልም ነው ያሉት። ለሀገርና ለሕዝብ መስዋዕት የከፈለን ሠራዊት መጠቀሚያ ለማድረግ መሞከር እንደማይገባም አሳስበዋል።

ጥያቄዎች አሉ ጥያቄዎችን የሚመለከተው አካል ይመልስ ነገር ግን ሀቅ ላይ ተመስርተን ሰላም መፍጠር አለብበን ነው ያሉት። አንድነት መፍጠር እና በሀቅ መመሥረት ጥያቄዎችን መፍታት ይገባል ብለዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበተከሰተው ድርቅ የታጠውን ምርት ለማካካስ የበጋ መስኖ ልማትን ዋነኛ የመፍትሔ አማራጭ አድርጎ እንደሚሠራ የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ገለጸ።
Next articleከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ወደ ባሕር ዳር እየገቡ ነው።