በተከሰተው ድርቅ የታጠውን ምርት ለማካካስ የበጋ መስኖ ልማትን ዋነኛ የመፍትሔ አማራጭ አድርጎ እንደሚሠራ የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ገለጸ።

36

ሰቆጣ: ሕዳር 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ቆላማ አካባቢዎች በድርቅ እንዳይጎዱ የውኃ ማጠራቀሚያ ግድብ እና ቦይ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል።

ይሁን እንጅ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት የግድቦቹ ብረቶች እና እቃዎች በመውደማቸው ምክንያት የበጋ መስኖ ልማትን በሙሉ አቅሙ ለመሥራት መቸገሩን በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የአብርገሌ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ገልጿል።

የኒየረ አቍ ከተማ ነዋሪው አቶ ዘውዱ ሳሙኤል እንደገለጹት ባለፋት ዓመታት የውኃ ቦዮችን በመጠቀም ቋሚ ተክል በማልማት ተጠቃሚ የነበሩ ቢኾንም ካናሉ በመጎዳቱ ከሚያለሙት 10 ሄክታር መስኖ አራት ሄክታሩን በጀኔሬተር ኀይል ለማልማት መገደዳቸውን ነው የተናገሩት።

የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ወይዘሮ መሠረት ወልደየስ ሁሉም ግድቦች አገልግሎት መስጠት ቢችሉ 600 ሄክታር መሬት በበጋ ማልማት ይቻል ነበር ብለዋል፡፡ አሁን ግን ሁለቱ ግድቦች በመጎዳታቸው በስድስት ቀበሌዎች ብቻ 45 ሄክታር መሬት እየለማ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

ኀላፊዋ እንደ አዲስ በ01 ቀበሌ ባለው ግድብ በጀኔሬተር ኀይል 18 ሄክታር እየለማ የሚገኝ ቢኾንም የፖምፕ እጥረት በወረዳው በመኖሩ ምክንያት በሙሉ አቅም ማልማት አለመቻሉን አስገንዝበዋል።

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የመስኖ ቆላማ አካባቢዎች ልማት መምሪያ ኀላፊ ተገኘ መብራቱ በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎች በመስኖ ልማት ተጠቃሚ እንዲኾኑ መምሪያው በትኩረት እየሠራ እና ከክልል ጋር እየተነጋገረ እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

አቶ ተገኘ ክልሉ በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች 184 የውኃ መሳቢያ ፖምፕ መስጠቱንም ተናግረዋል፡፡በዚህ ሳምንትም ለወረዳዎች እንደሚከፋፈል ነው ያረጋገጡት።

በቀጣይም በመስኖ ልማት የተከሰተውን ድርቅ አርሶ አደሮች እንዲቋቋሙ የበጋ መስኖ ልማትን ዋነኛ የመፍትሔ አማራጭ በማድረግ እንደሚሠራም ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጥያቄ አለኝ ተብሎ ሀገር አይፈርስም፤ ሕዝብ አይበተንም” ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ
Next article“የቆምነው ለሠንደቅ ዓላማ እና ለኢትዮጵያ ነው” ሌትናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ