“ጥያቄ አለኝ ተብሎ ሀገር አይፈርስም፤ ሕዝብ አይበተንም” ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ

111

ባሕር ዳር: ኅዳር 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በባሕር ዳር ከተማ እየተካሔደ ያለውን ውይይት የመሩት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ግጭት የሕዝብን መከራ እንደሚያሰፋ ተናግረዋል።

ሰላምን በማስቀደም መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል። ጥያቄ አለኝ ተብሎ ሀገር አይፈርስም፣ ሕዝብ አይበተንም ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ሕዝብን በተዛባ መረጃ ማወናበድ እና መከራውን ማብዛት እንደማይገባም አሳስበዋል።

ሕዝብ በሀሰተኛ ወሬ ጠማቂዎች በችግር እንዲኖር እየተደረገ መኾኑንም አንስተዋል። የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች በሕጋዊ መንገድ እንዲፈቱ በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

ችግሮቹ በዘላቂነት እንዲፈቱ እየሠራን ነውም ብለዋል። በሀገር መከላከያ ሠራዎት ላይ ያልተገባ ስም መሥጠት፣ ጥላቻ መንዛት እና የአንድ አካል አስመስሎ ማራገብ መታረም እንደሚገባውም አመላክተዋል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገር የመጨረሻው ምሽግ መኾኑንም ተናግረዋል።

የተፈናቀሉ ወገኖች በዘላቂነት እንዲመለሱ እየተሰራ መኾኑንም አመላክተዋል። የዜጎችን ደኅንነት መጠበቅ እና ዋስትና መሥጠት ይገባልም ነው ያሉት። ያጡትን ንብረት እና መሬት ማግኘት እንደሚገባቸውም አመላክተዋል። በተፈናቃዮች ዙሪያ መፍትሔዎች እንደሚኖሩም ገልጸዋል።

ሰላማዊ ውይይቶችን መንግሥት አልከለከለም፤ አይከለክልም ነው ያሉት። የአማራ ሕዝብ መብት እና ጥቅም እንዲጠበቅ እንሠራለን ያሉት አቶ አረጋ የጋራ ሀገር እንድትኖር መሥራትም ይገባል ነው ያሉት።

ዘላቂ ሰላም እንዲኖር ሕዝቡ እንዲሠራም ጥሪ አቅርበዋል። ግጭት የአማራ ክልልን ምጣኔ ሃብት እንደሚጎዳ ነው የተናገሩት። ሁሉም ለሰላም መሥራት ይገባዋልም ብለዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ለዘላቂ ሰላም ወሳኙ ነገር ውይይት ነው” የባሕርዳር ከተማ ነዋሪዎች
Next articleበተከሰተው ድርቅ የታጠውን ምርት ለማካካስ የበጋ መስኖ ልማትን ዋነኛ የመፍትሔ አማራጭ አድርጎ እንደሚሠራ የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ገለጸ።