“ለዘላቂ ሰላም ወሳኙ ነገር ውይይት ነው” የባሕርዳር ከተማ ነዋሪዎች

55

ባሕር ዳር: ሕዳር 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ ከባሕርዳር ከተማ ነዋሪዎች ጋር በወቅታዊ የጸጥታ ጉዳዮች እየተወያዩ ነው።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የከተማዋ ነዋሪዎች የተለያዩ ሃሳቦችን አንስተዋል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያ መከታ ነው ብለዋል።

ፋኖ በታሪኩ ለሀገር የቆመ የአባቶች የማንነት መገለጫ ነው ያሉት ነዋሪዎቹ በፋኖ ስም የሚነግዱ እና ሕዝብን የሚያሰቃዩ መኖራቸውንም አመላክተዋል።

በኢትዮጵያ መፈረጅ እና ማግለል መኖሩን የተናገሩት ነዋሪዎቹ ፍረጃ ነገሮች እንዲባባሱ እና ግጭት እንዲሰፋ ማድረጉንም አመላክተዋል። ጠቅላላ የኾነ ፍረጃ የታሪክ ስም የኾነውን ያጠለሻል፣ ሰላምም አያመጣም ብለዋል።

ከጦርነት አዙሪት እንውጣ ችግሩ በውይይት ይፈታ፣ ልጆቻችን በስቃይ እንዲኖሩ አንፈልግም ነው ያሉት። ሕግ ይከበር፣ አንድነታችንን እንጠብቅ፣ ለሰላም እንታገልም ብለዋል።

እውነትን ደፍረን ከዚህ በኋላ ሊመጣ የሚችለውን ችግር እንመክተው፣ ከዚህ በኋላ የንፁሐን ሞት እንዳይኖር እንሥራም ብለዋል።

ለሕዝብ ትክክለኛ ፍትሕ ስጡ፣ ሕዝቡ ፍትሕ ተጠምቷል ነው ያሉት። ለሀገር ለሚታገል የሚገባውን ማድረግ፣ለሀገር የማይጠቅመውን ደግሞ ሕጋዊ መፍትሔ መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።

ያለፈው አልፏል ለሚመጣው በትክክለኛው መንገድ መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል። በቀውሱ የኑሮ ውድነት፣ የሥራ አጥነት ማስፋፋት እና ድህነት እየሰፋ መሄዱንም ገልጸዋል።

ጦርነት መሠረተ ልማትን ከማውደም፣ የሕዝብን እንቅስቃሴ ከመገደብ የዘለለ መፍትሔ እንደሌለውም አንስተዋል።

የእርስ በእርስ ጦርነት የአማራ ሕዝብ የታሪክ መገለጫ አይደለም፤ አማራ ሰላም እንዳይሆን የሚሠሩትን መታገል እና ታሪኩን የሚመጥን ሥራ መሥራት ይገባል ነው ያሉት።

የሃይማኖት አባቶች በየቦታው ለሰላም እንዲሠሩ እና እንዲያስታርቁም ጠይቀዋል። ለሰው ልጆች የሚጠቅመውን እና የሚበጀውን ማስተማር እንደሚገባቸውም አመላክተዋል። ለሀገርና ለሕዝብ የሚጠቅመውን ብቻ ማድረግ ይገባል ብለዋል። በአመጽ ከሚመጣ መፍትሔ በሰላም የሚመጣ መፍትሔ የተሻለ መኾኑንም ገልጸዋል።

በተደጋጋሚ የሚነሱ ግጭቶች ክልሉን በእጅጉ መጉዳቱንም ጠቅሰዋል። የአማራ ክልል በጦርነቱ የወደመበትን መገንባት እና ወደ ተሻለ ደረጃ መሸጋገር እንጂ ወደ ሌላ ጦርነት መግባት አይገባውም ብለዋል።

ሰላምን በአንድነት መጠበቅ ይገባናል ሲሉም ሀሳባቸውን ገልጸዋል። ለዘላቂ ሰላም ወሳኙ ነገር ንግግር ነውም ብለዋል ነዋሪዎቹ።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የአማራ ሕዝብን ጥያቄዎች ለመፍታት እርስ በእርስ መገዳደል አያስፈልግም” የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው
Next article“ጥያቄ አለኝ ተብሎ ሀገር አይፈርስም፤ ሕዝብ አይበተንም” ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ