
ባሕር ዳር: ኅዳር 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ከክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው መወቃቀስ እና እርስ በእርስ መጠቋቆም የሕዝብን አንድነት ከመጉዳት የዘለለ ያመጣው ጥቅም የለም ብለዋል።
ለአማራ ሕዝብ መብት፣ ሰላም እና አንድነት መረጋገጥ ራሱ የአማራ ሕዝብ ቀዳሚ መኾን እንደሚገባው አንስተዋል።
የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ጉዳት ማድረሱን የተናገሩት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ከዚህ በኋላ ግጭትን የሚቋቋም ሕዝብ የለም ነው ያሉት።ግጭት የሚያባብሱ ጉዳዮችን መተው እና ስለ ሰላም መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል።
ድምጽን አጥፍቶ መሥራት እና የሕዝብን ጥያቄ መመለስ አስፈላጊ መኾኑንም ገልፀዋል።
የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመፍታት አስቀድሞ ለሰላም እንቅፋት የኾኑ ችግሮችን መፍታት ይገባል ነው ያሉት። የኑሮ ውድነትን ለመታገል እና ሌሎች አንገብጋቢ ችግሮችን ለመፍታት ለሰላም በአንደነት መሥራት ያስፈልጋልም ብለዋል።
የባሕር ዳር ከተማ ሰላም የሚጸናው የክልሉ ሰላም ሲጸና መኾኑንም አንስተዋል። “የአማራ ሕዝብን ጥያቄዎች ለመፍታት እርስ በእርስ መገዳደል አያስፈልግም” ብለዋል አቶ ጎሹ። ችግሮቻችን በውይይት እና በንግግር መፍታት ያስፈልጋል ነው ያሉት። መገዳደል ችግሮችን ከማባበስ የዘለለ ያመጣው ለውጥ አለመኖሩንም አንስተዋል።
በከተማዋ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር አለ ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ሕዝብን ያማረሩ ችግሮችን ለመፍታት እየሠራን ነው፤ እንሠራለንም ብለዋል። የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሩን ለመፍታት ዘመናዊ ሥርዓት እንዘረጋለንም ነው ያሉት። የኑሮ ውድነትን የሚያባብሱ ችግሮችንም እንፈታለንም ብለዋል።
ነዋሪዎችን እያማረረ ያለውን የቤት ኪራይ ጭማሪ እልባት እንደሚያገኝም ጠቁመዋል። ወጣቶች የሥራ እድል ተጠቃሚ እንዲኾኑም እየተሰራ ነው ተብሏል።
ባሕር ዳር መሠረተ ልማቶቿ የተሟሉላት እና የነዋሪዎቿ ችግር የተፈቱላት ተወዳደሪ ከተማ እንድትኾን እንሠራለንም ብለዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!