ችግር ላይ የወደቁ ሕጻናትን ሁሉም እንዲደግፍ ተጠየቀ።

32

ባሕር ዳር: ኅዳር 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “ምርኩዝ በጎ አድራጎት ማኅበር” በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ፋሲሎ ክፍለ ከተማ ለችግር ለተጋለጡ 100 ሕጻናት ድጋፍ አድርጓል።

ማኅበሩ በ200 ሺህ ብር ወጭ ማኮሮኒ፣ ዘይት እና የንጽሕና መጠበቂያ ሳሙና ነው ድጋፍ ያደረገው።

የማኅበሩ አስተባባሪ ሽኩር አሕመድ እንዳሉት ድርጅቱ ከተመሰረተ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ 150 ለችግር የተጋለጡ ቤተሰቦች 1 ሺህ 50ዐ ብር በቋሚነት ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

ባለፉት ሦስት ወራት 600 ለሚኾኑ ሰዎች የምግብ ድጋፍ አድርጓል። ለ1 ሺህ 760 ተማሪዎች ደግሞ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ነው የገለጹት።

የነገ ሀገር ተረካቢ ሕጻናትን መደገፍ የሁሉም ሰው ኀላፊነት ሊኾን ይገባልም ብለዋል።

የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች ሕጻናት ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሰብለ ዘውዱ እንዳሉት በክልሉ በተከሰተው የሰላም መደፍረስ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለችግር ተጋልጠዋል።

በተለይም ደግሞ ሕጻናት እና ሴቶች የችግሩ ሰለባ ኾነዋል።

በከተማ አሥተዳደሩ ለ461 ሕጻናት በቋሚነት ድጋፍ እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል።

ማኅበሩ እያደረገ ያለው ድጋፍ የመረዳዳት ባሕልን የሚያጎለብት መኾኑንም አንስተዋል።

ይሁን እንጂ ድጋፉ ካለው ችግር ስፋት አኳያ በቂ ባለመኾኑ ማኅበረሰቡ፣ የተለያዩ ድርጅቶች እና ተቋማት ችግር ላይ ለወደቁ ሕጻናት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ክልል ወሳኝ ኩነቶች አገልግሎት በክልሉ የተከሰተው የጸጥታ ችግር በሥራው ላይ እንቅፋት እንደፈጠረበት አስታወቀ፡፡
Next article“የአማራ ሕዝብን ጥያቄዎች ለመፍታት እርስ በእርስ መገዳደል አያስፈልግም” የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው