
ባሕር ዳር: ኅዳር 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የክልሉ ወሳኝ ኩነቶች አገልግሎት የዕቅድ፣ በጀት፣ ዝግጅት እና ክትትል ዳይሬክተር ዋለ ቅዱስ አገልግሎቱ ለሕዝብ ተደራሽ ከኾነባቸው 20 ዞኖች እና ከተሞች መካከል በሩብ ዓመቱ ሥራውን ማከናወን የቻለው በሰባቱ ብቻ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
አገልግሎቱ በሩብ ዓመቱ በክልል ደረጃ 830 ሺህ 150 ኩነቶችን በወቅቱ፣ በጥራት እና በብቃት ለመመዝገብ ቢያቅድም በጸጥታ ችግር ምክንት የፈጸመው ግን 24 ሺህ 779 ብቻ መኾኑን አስረድተዋል፡፡ ይህም አፈጻጸሙ 52 ነጥብ 84 በመቶ ብቻ ነው ብለዋል አቶ ዋለ፡፡
ዳይሬክተሩ እንዳሉት የኩነቶች ምዝገባ በክልሉ የሚኖሩ ዜጎች የማንነት ጉዳይ በመኾኑ መንግሥት በሰጠው ልዩ ትኩረት የምዝገባ እና የመረጃ ልውውጥ ሥርዓቱን ለማዘመን የቅድመ ዝግጅት ሥራው እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡
የክልሉ ኩነቶች አገልግሎት ተደራሽ ከኾነባቸው 4 ሺህ 18 የምዝገባ ጣቢያዎች መካከል በ1 ሺህ 205 ቀበሌዎች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ ምዝገባ እና የመረጃ ልውውጥ ሥርዓት ለመዘርጋት ግብዓት እየተሟላ እንደሚገኝም አብራርተዋል፡፡
የአማራ ክልል ወሳኝ ኩነቶች አገልግሎቱ የጋብቻ፣ ልደት፣ ፍቺ፣ ሞት፣ ጉዲፍቻ፣ አባትነትን በፍርድ ቤት የማወቅ እና ልጅነትን የመቀበል ምዝገባ እያከናወነ ይገኛል፡፡
የአማራ ክልል ወሳኝ ኩነቶች አገልግሎት ሥራ የጀመረው ሐምሌ 30 /2008 ዓ.ም እንደኾነ ከአገልግሎቱ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡
ዘጋቢ፡- ሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!