“ሰላማዊው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እንደበፊቱ ሁሉም ዜጋ በሰላም የሚኖርበት ኾኖ እንዲቀጥል እንሠራለን” ርእሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ

43

አዲስ አበባ: ኅዳር 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዛሬ የፌዴራል መንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ አፈጉባኤዎች፣ የሁሉም ክልል ርእሳነ መሥተዳድሮች፣ የክልሉ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በተገኙበት ይፋዊ የሥራ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት እያካሄደ ነው።

የክልሉ ርእሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ “የተለያዩ እንቅፋቶችን አልፈን ዛሬ የክልሉ ይፋዊ የሥራ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ላይ ደርሰናል፤ ሁላችሁም አንኳን ደስ አላችሁ” ብለዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የ32 ብሔረሰቦች እና የተለያዩ ወጎች እና ሥርዓቶች ባለቤት እንደኾነም አስረድተዋል፡፡ ክልሉ የገፀ ምድር እና የከርሰ ምድር ሀብቶች ባለቤት እንደኾነም ነው ያብራሩት።

የክልሉን ሕዝብ ጥያቄዎች ለመመለስ የተለያዩ ሥራዎች እንደሚከናወኑም ነው የገለጹት፡፡

ዛሬ ክልሉ እውን አንዲኾን እና የሕዝቡ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ላደረጉ ለመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ ለፓርቲ አመራሮች፣ ለተለያዩ የኅብረሰተብ ክፍሎች፣ ለጸጥታ ተቋማት እና ለመገናኛ ብዙኀን ምሥጋና አቅረበዋል።

ክልሉ በወንድማማችነት እና ሰላምን መሰረት አድርጎ የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ የተቋቋመ ስለመኾኑም ነው ያብራሩት።

አካባቢው ሰላም የነገሰበት፤ በፍቅር የሚኖርበት መኾኑን ያስታወሱት ርእሰ መሥተዳድሩ ማንኛውም ዜጋ በእኩልነት ሠርቶ የሚኖርበት ክልል አንዲኾን በቁርጠኝነት እንደሚሠራም አረጋግጠዋል፡፡ “ሰላማዊው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እንደበፊቱ ሁሉም ዜጋ በሰላም የሚኖርበት ኾኖ እንዲቀጥል እንሠራለን” ሲሉም ርእሰ መሥተዳድሩ ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበ4ኛው ዙር የአቅም ግንባታ ሥልጠና የሚሳተፉ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ጎንደር ከተማ እየገቡ ነው።
Next articleየአማራ ክልል ወሳኝ ኩነቶች አገልግሎት በክልሉ የተከሰተው የጸጥታ ችግር በሥራው ላይ እንቅፋት እንደፈጠረበት አስታወቀ፡፡