
ጎንደር: ኅዳር 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ቀጣና በሁለተኛው ዙር በተሰጠው የተሃድሶ ሥልጠና 150 ሰልጣኞች ሥልጠናቸውን ማጠናቀቃቸውን የሥልጠናው አስተባባሪ አቤል መብት አስታውቀዋል።
በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት ተከትሎ በጎንደር ቀጣና በተለያየ መንገድ የተጠረጠሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በሕግ ጥላ ሥር ቆይተው የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው ወደ ኅብረተሰቡ ተቀላቅለዋል።
በማዕከሉ የተሰጠውን ሥልጠና ያጠናቀቁ ሰልጣኞች በቆይታቸው ሥልጠናው የሰላምን አሥፈላጊነት በጉልህ የተረዳንበት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ሥልጠናውን ያጠናቀቁት ወጣቶች በተሰጣቸው ሥልጠና መሰረት የሕዝቡን ሰላም በመጠበቅ የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መኾናቸውን ተናግረዋል።
የጎንደር ቀጣና የተሃድሶ ሥልጠና አስተባባሪ አቤል መብት ለሁለተኛ ዙር በተሠጠው ሥልጠና 150 ሰልጣኞች መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡ ሥልጠናው ክልላዊ ሰነድን መሠረት ያደረገ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡
ሰልጣኞች በነበራቸው ቆይታ የተፈጠረላቸውን ግንዛቤ መሰረት በማድረግ የሰላም እና የልማት አምባሳደሮች ይኾናሉ ሲሉም ተናግረዋል።
የጎንደር ቀጣና ኮማንድ ፖስት ተወካይ ሌተናል ኮሎኔል ቢያ አባ ሜንጫ ሠልጣኞች ከሥልጠና በኋላ ኀላፊነት የተጣለባቸው መኾኑን አብራርተዋል፡፡ ሰላምን መሠረት ያደረገ ሥልጠና መሠጠቱንም ገልጸዋል።
አንድነትን ይበልጥ በማጠናከር እና በኢትዬጲያዊነት መንፈሥ ለሀገር ሰላም ቅድሚያ በመሥጠት የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- መሠረት ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!