
አዲስ አበባ: ኅዳር 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከነሐሴ 15/2015 ዓ.ም ጀምሮ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ዕውቅና ማግኘቱ ይታወቃል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 12ኛ የፌዴሬሽኑ ክልል ኾኖ የተመሰረተው ይህ ክልል ዛሬ ይፋዊ ሥራ ይጀምራል፡፡ እንዲኹም ከሌሎች የፌዴሬሽኑ ክልሎች የተደረገለትን ድጋፍ ይረከባል፡፡
ክልሉ 6 ብዝኀ ከተሞች እንዲኖሩት ኾኖ የተዋቀረ ሲኾን
👉 ወላይታ ሶዶ፦ የፖለቲካ እና የአሥተዳደር ማዕከል
👉 አርባምንጭ፦ የኢኮኖሚ እና ሕግ አውጭ ማዕከል
👉 ኮንሶ ካራት ከተማ፦ የሕገ መንግሥት ትርጉም ማዕከል
👉 ሳውላ፦ የፍትህ ተቋማት ማዕከል
👉 ጂንካ፦ የማኅበራዊ ክላስተር ማዕከል
👉 ዲላ፦ የግብርና እና ገጠር ልማት ማዕከል
ክልሉ 32 ብሔረሰቦችን ያቀፈ ሲኾን በ12 ዞኖች ተደራጅቷል፡፡ የጸደቀ ሕገ መንግሥት አዘጋጅቷል።
በክልሉ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ የቱሪዝም ሀብቶች ያሉት የራሱ የኾነ ባሕል እና ቅርስ ባለቤትም ነው፡፡ በዋናነት ከሚጠቀሱት ውስጥ የጌዲዮ መልካም ምድር፣ የኮንሶ ርከን፣ የጁራ ፏፏቴ፣ የቡስካ፣ የዳሞታ፣ ጉጌ፣ የዴሎ ተራራዎች፣ የአባያ እና ጫሞ ሐይቆች፣ የነጭ ሳር፣ የማዜ፣ የኦሞ እና የማጎ ብሔራዊ ፓርኮች ባለቤት ነው፡፡
ሁሉም ዞኖች የራሳቸው የኾነ የሽምግልና፣ የግጭት መፍቻ ሥነ ሥርዓት፣ የዘመን መለወጫ በዓል እና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት ነው።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተፈጥሮ ሀብቶች የታደለ፤ ለኢንቨስትመንት ምቹ ክልል ሲኾን በግብርና እና በግብርና ኢንዱስትሪ፣ በሆቴል እና ቱሪዝም፣ ለእንስሳት እርባታ እና በማእድን ልማት ምቹ የኾኑ ሀብቶች ያሉት ክልል ነው።
ክልሉ ዛሬ በይፋ ሥራውን ይጀምራል፡፡
ዘጋቢ ፡- አንዷለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
