“የአባቶቻችን ብልሐት እና የወንድሞቻችን ጉልበት ለሀገር እድገት መጠቀም ይገባል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

45

ባሕር ዳር: ኅዳር 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ከባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ነዋሪዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ እየመከሩ ነው።

በመድረኩ መልእክት ያስተላለፉት ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ “የአባቶቻችን ብልሐት እና የወንድሞቻችን ጉልበት ለሀገር እድገት መጠቀም ይገባል” ብለዋል። በክልሉ በተፈጠረው የሰላም እጦት ችግር የክልሉ ሕዝብ እና መንግሥት ከመደበኛ ሥራው ይልቅ በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች መጠመዱን አመላክተዋል።

ክልሉ ላለፉት ወራት በቀውስ ውስጥ እንደቆየ የገለጹት ርእሰ መሥተዳድሩ ከምክር እስከ ሕግ ማስከበር መሥራት ይገባልም ብለዋል። የጸጥታ ችግሮችን በመወያየት መለየት እና መግባባት ይገባል ነው ያሉት።

ሰላም ማምጣት የአንድ ወገን ጉዳይ ብቻ አይደለም ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ሰላም የሁሉም በመኾኑ ሁሉም ለሰላም መሥራት ይኖርበታል ብለዋል።

የአማራ ክልል በሰሜኑ ጦርነት ከፍተኛ ጉዳት እንደረሰበትም ርእሰ መሥተዳድሩ በመልዕክታቸው አንስተዋል። ጦርነቱ የፈጠረው ከፍተኛ ውድመት በምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ ወደኋላ የመለሰ እንደነበርም ተናግረዋል።

ርእሰ መሥተዳድሩ በመልዕክታቸው ሕዝብን ማወክ እንደጀግንነት እና ሠርቶ መግባት ለሕዝብ እንዳለመቆርቆር የሚታይበት ሁኔታ መኖሩንም ተናግረዋል። ልዩነትን በአፈ-ሙዝ ለመመለስ መሞከር ክልሉን እንደሚያከስርም አመላክተዋል።

በአማራ ክልል የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ክልሉን ያወድም ካልኾነ በስተቀር ሌላ መፍትሔ አይኖረውም ብለዋል። ከራስ በላይ ማሰብ የሚጠይቅ እና መፍትሔ የምናፈላልግበት ወቅት ላይ ነንም ነው ያሉት።

የክልሉ አንድነት እና ሰላም አንዲጠናከር መወያየት እንደሚገባም አመላክተዋል።

የመንግሥት ስልጣን ሁሌም የሚኖር አይደለም ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ሁሌም የሚኖረው እና ዋናው ዓላማችን የሕዝብ ሰላም፣ የክልሉን ሕዝብ አንድነት እንዴት እናስቀጥል፣ ለኢትዮጵያስ ምን እናበርከት፣ ሀገርንስ እንዴት እናስቀጥል የሚለው ነውም ብለዋል።

ሁሌም መጨነቅ የሚገባው ለክልሉ ሰላም፣ አንድነት እና የሀገር ቀጣይነት መኾን አለበትም ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ በመልእክተታቸው።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች በወቅተዊ ጉዳዮች ዙሪያ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በተገኙበት እየመከሩ ነው።
Next articleአዲስ የተመሰረተው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዛሬ ሥራውን በይፋ ይጀምራል፡፡