የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች በወቅተዊ ጉዳዮች ዙሪያ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በተገኙበት እየመከሩ ነው።

46

ባሕር ዳር: ኅዳር 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በውይይቱ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የአማራ ሕዝብ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ታላቅ አሻራ ያለው መኾኑን ገልጸዋል።

የአማራ ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመኾን ኢትዮጵያ ነፃነቷን ጠብቃ እንድትኖር እና እንድትከበር ያደረገ ሕዝብ መኾኑንም ተናግረዋል። በተለይም ባለፉት ዓመታት በተሠራው ያልተገባ ትርክት በሕዝብ መካከል ጥርጣሬ እንዲፈጠር፣ አንድንት እንዲቀንስ መደረጉንም ገልፀዋል።

የሕዝብን አንድነት ለመመለስ እና ለማጠናከር እየተሠራ መኾኑን የተናገሩት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር እንደሚመለሱም አመላክተዋል።

በክልሉ በተሠራው ሥራ አንፃራዊ ሰላም እየተፈጠረ መኾኑንም አመላክተዋል። በከተማዋ እና በክልሉ እየተሻሻለ የመጣው ለውጥ ዘላቂ እንዲኾን መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል።

በሰላም እጦት ችግር ምክንያት የልማት ሥራዎች መስተጓጎላቸውን፣ የኑሮ ውድነት መባባሱን እና ኢንዱስትሪዎች ሥራ ማቆማቸውንም ተናግረዋል።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ችግሮቻችንን በውይይት እና በሰላማዊ መንገድ መፍታት ይገባናልም ብለዋል።

በምክክር መድረኩ ከርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በተጨማሪ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የርእሰ መሥተዳደሩ የሕዝብ ግንኙነትና የአደረጃጀት ዘርፍ አማካሪ ይርጋ ሲሳይ፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ጉዳዮች አስተባባሪ እና የሰላምና የጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ደሳለኝ ጣሰው፣ የሰሜን ምዕራብ እዝ አዛዥ ሌትናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ፣ የምሥራቅ እዝ አዛዥ ሌትናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ፣ ጀኔራል መኮንኖች እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየቻይና ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ በአማርኛ ቋንቋ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ሊያስመርቅ ነው።
Next article“የአባቶቻችን ብልሐት እና የወንድሞቻችን ጉልበት ለሀገር እድገት መጠቀም ይገባል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ