ኢትዮጵያ በ28ኛው የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ላይ ተሞክሮዋን እንደምታካፍል ተገለጸ፡፡

55

አዲስ አበባ: ኅዳር 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በ28ኛው የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ላይ በአረንጓዴ አሻራ እና መሰል ሥራዎቿ ላይ ተሞክሮዋን እንደምታካፍል የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ገለጿል፡፡

በተባበሩት አረብ ኢምሬት ለ28ኛ ጊዜ የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ይካሄዳል፡፡ ከኅዳር 20/2016 ዓ.ም እስከ ታኅሣሥ 2/ 2016 ዓ.ም በሚካሄደው ጉባዔ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ120 በላይ ሀገራት እንደሚሳተፉ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አሳውቋል።

ጉባዔው በሦስት ምዕራፎች የተከፈሉ የተለያዩ ክንውኖች እንደሚኖሩትና የሀገራት መሪዎችም በአየር ንብረት ለውጥ ፖሊሲዎች ላይ ይመክራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ሚኒስትር ዴኤታ ነመራ ገበየሁ (ዶ.ር) ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ከፍተኛ ዝግጅት ማድረጓን የጠቀሱት ዶክተር ነመራ ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን በአየር ንብረት ለውጥ የደረሰችበት የሥራ አፈጻጸም በጉባዔው ላይ የሚቀርብ ይኾናል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ፣ በስንዴ ልማት፣ በምግብ ሥርዓት ላይ የሠራቻቸውን ሥራዎች በተመለከተ በዓለም አቀፍ መድረኩ ላይ ተሞክሮዋን እንደምታካፍል አስረድተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይም ከተለያዩ የልማት አጋሮች ጋር ውይይቶች የሚካሄዱ መኾናቸውን ሚኒስትር ዴኤታው አስገንዝበዋል፡፡

በጉባኤው በተለያዩ ጊዜያት በአየር ንብረት ለውጥ ለተጎዱ ታዳጊ ሀገራት ድጋፍ ለማድረግ የተገቡ ቃሎች ትግበራ ላይ ምክክር እንደሚደረግም በመግለጫው ተጠቅሷል።

ዘጋቢ፡- ራሔል ደምሰው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በጎጃም የገጠመንን መሠረታዊ የሰላም ችግር ሕዝቡ ራሱ የሰላሙ ባለቤት ሆኖ ለመፍታት የበኩሉን መወጣት የሚያስችል ውይይት በሰሜን ጎጃም ዞን በመራዊ ከተማ ተካሂዷል” ሌተናል ጀኔራል መሐመድ ተሰማ
Next articleየቻይና ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ በአማርኛ ቋንቋ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ሊያስመርቅ ነው።