
ባሕር ዳር: ኅዳር 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ወጣት መንግሥቱ አምላኩ ይባላል። የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ እና የባጃጅ አሽከርካሪ ነው። ወጣቱ እንደሚለው ሠርክ ጠዋት ላይ መነሻውን በተለምዶ “የተባበሩት” እየተባለ ከሚጠራው ሥፍራ አድርጎ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሜሪታይም አካዳሚ አካባቢ በኮንትራት የሚያደርሳቸው ደንበኞች አሉት።
ታዲያ በተለይም ቅዳሜ እና እሑድ ማለዳ ላይ ከመነሻው እስከ መድረሻው ድረስ ሲሄድና ሲመለስ ቢያንስ ስምንት ቦታ ላይ አስፋልቱን በድንጋይ ዘግተው እግር ኳስ የሚጫወቱ አልፎ አልፎም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚሠሩ ግለሰቦች ሥራውን ያስተጓጉሉበታል።
ወጣቱ እንደሚለው ንጋት ላይ የተሽከርካሪውን ሞተር አስነስቶ ሥራውን ሲጀምር የሚያሳስበው እና የሚያስጨንቀው ነገር መንገድ ዘግተው ስፖርታዊ ጨዋታ የሚያከናውኑ ግለሰቦች ጉዳይ ነው። የሁኔታው ለከት አለመኖርም በምሬት “መንግሥት የለም እንዴ ?!” እስከ ማለት አድርሶታል።
ወጣቱ እንደሚለው በአንድ ወቅት መንገድ ላይ ኳስ በሚጫወቱ ግለሰቦች መሐል ባጃጁን ለማሳለፍ ሲሞክር ኳስ ለመመለስ ሩጦ የመጣ ግለሰብን ገጭቶ ይጥለዋል። በድርድር አደጋ የደረሰበትን ግለሰብ ለማሳከም ይስማማል። ለዚህም በርካታ ገንዘብ ከማውጣቱ ባሻገር አደጋ የደረሰበት ግለሰብ ዘመዶች ቀን ጠብቀው ይጎዱኛል በማለት እሱ መሥራት እየቻለ ሹፌር በመቅጠር ለአላሥፈላጊ ወጭ የተዳረገበት ወቅት እንደነበር ጠቁሟል።
ሌላው የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ልዑል ገበየሁ እንደሚሉት በአካባቢያቸው የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራ ባለመኖሩ ለጤናቸው የአካል ብቃት የሚሠሩት በጌጠኛ የድንጋይ ንጣፍ መንገድ ላይ ነው። ለምን ሲባሉ “የት ሂጄ ልሥራ” ምላሻቸው ነው።
አቶ ልዑል ጊዜያዊ ያሉትን መፍትሔም ጠቁመዋል። እዚህም እዚያም በየመንገዱ ዳር ለመኪና ፓርኪንግ ሥራ በጊዜያዊነት ቦታ ተፈቅዶ ውጤታማ ሥራ እየተከናወነ ነው ባይ ናቸው። ታዲያ የከተማው ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያው ይህን መልካም ተመክሮ ወደ ስፖርቱ አምጥቶ መሰል ቦታዎችን ለአካል ብቃት መሥሪያ አስፈቅዶ ሕዝባዊ ቢያደርግ እጥረቱ እና እየደረሰ ያለው ችግር ይቃለላል ይላሉ።
አቶ ሀብታሙ ሳሉዓለም ቀደም ሲል ይኖር በነበረበት የጎንደር ከተማ ውስጥ በአንድ ቡድን ውስጥ የእግር ኳስ ተጫዋች እንደነበር አስታውሷል። እሱ እንደሚለው ታዲያ ኑሮውን ባሕር ዳር ባደረገ ማግሥት ለጤናቸው ይበጅ ዘንድ ጥዋት ጥዋት ከጓደኞቹ ጋር በአካባቢያቸው የእግር ኳስ ሜዳ ባለመኖሩ አስፋልት በድንጋይ ዘግተው ለመጫወት መገደዳቸውን ተናግሯል።
“ማንም ሰው አስፓልት ላይ ተሽከርካሪን እየታከከ የሚጫወተው አቧራ ተጸይፎ አይደለም፤ በየአካባቢው የሚጫወትበት ሜዳ ባለመኖሩ እንጂ። ሥለዚህ ይላሉ አቶ ሀብታሙ “የከተማ አሥተዳደሩ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችን በአማካይ ሥፍራ ቢሠራ እኛን ከአደጋ ታድጎ ስፖርቱንም ማሳደግ ይችላል፤ አሽከርካሪዎችም በእኛ ጦስ አይቸገሩም” ብለዋል።
አቶ ዘላለም ጌጤነህ የስፖርት ሳይንስ መምህር እና የታዳጊዎች እግር ኳስ አሠልጣኝ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት ባሕር ዳር ከተማ ከነዋሪዋ ቁጥር አንጻር ያሏት የማዘውተሪያ ሥፍራዎች ጥቂት ናቸው። በየአካባቢው ለስፖርት ተብሎ የታጠረ ቦታ ቢኖርም ለስፖርታዊ ጨዋታ በሚበጅ መልኩ ባለመዘጋጀቱ የጤና ስፖርት አዘውታሪዎችና ወጣቶች አስፓልት ላይ እንዲሠሩ ተገድደዋል ብለዋል።
መምህር ዘላለም እንደሚሉትም መፍትሔው የሚመለከተው አካል ኀብረተሰቡን አስተባብሮ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችን መገንባት ብቻ ነው ሲሉ ሀሳባቸውን አካፍለዋል።
በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ የስፖርት ሜዳ ዝግጅት ባለሙያ አቶ መልሰው ወርቁ እንዳሉት በከተማዋ ሰባት ካርታ ያላቸው የማዘውተሪያ ሥፍራዎች ብቻ ናቸው ያሉት። ይህ አሃዝ የግለሰቦችን ጥያቄ ተገቢነት ይናገራል ይላሉ። ለመፍትሔውም ታጥረው የተቀመጡትን ቦታዎች ማጠናቀቅ ግድ እንደሚል ተናግረዋል። ለዚህ ደግሞ ሃብት እየተፈላለገ ነው። እስካሁን ግን ለዚህ ተብሎ የተያዘ በጀት እንደሌለ ባለሙያው አልሸሸጉም፤ ይሁንና ያለንበትን ወቅት ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ተገቢም እንደኾነ ነው የገለጹት። ባለሙያው አክለውም አዳዲስ የመዝናኛ እና የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ተገንብተው በመጠናቀቅ ላይ ስለኾኑም ከርክክብ በኋላ ችግሩ በመጠኑ ይቀንሳል ብለዋል። ቀድም ሲል “አሮጌው ዲፖ” እየተባለ በሚጠራው አካባቢ እየተሠራ ያለውን የጨዋታ ሜዳ በመጠቆም። “ዲያስፖራ መንደር” አካባቢም እየተገነባ ያለን ሁለገብ የመጫዎቻ ሜዳ በማስታወስ።
ዘጋቢ፡- ሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!