በሰሜን ጎጃም ዞን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሕዝባዊ ውይይት ተካሄደ።

37

ባሕር ዳር: ኅዳር 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በጎጃም የገጠመውን መሰረታዊ የሰላም ችግር ሕዝቡ ራሱ የሰላሙ ባለቤት ሆኖ ለመፍታት የበኩሉን መወጣት እንዲችል የሚያደርግ ውይይት በሰሜን ጎጃም ዞን በመራዊ ከተማ ተካሂዷል ፡፡

በውይይቱ ላይ የምስራቅ ዕዝ አዛዥና የጎጃም ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሌተናል ጀኔራል መሐመድ ተሰማ ፍላጎታቸውን በኃይል ለማሳካት የሚፈልጊ አካላት የሚያከናውኑት የዕብሪት ተግባር ለሕዝብ ስለማይጠቅም ሊቆም ይገባል ብለዋል። ይህ አካሄድ የኢትዮጵያን ሕዝቦች አንድነት አደጋ ላይ የሚጥል ድርጊት ነው፤ ሁከትና ብጥብጥንም የሚያነግስ ነው፤ ስለዚህ የመራዊ ሕዝብ በአንድነት ቆሞ ሊታገለው ይገባል ብለዋል ፡፡

በአንድ በኩል የድህነት ተራራን ለመናድ ህዝቡ እየታተረ፣ እየሠራ፣ ለውጥ እያሳየ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ወደ ኋላ የሚጎትትና የሚያበላሽ ጽንፍ የወጡ እንቅስቃሴዎች እየታዩ እና ለኢትዮጵያ የጸጥታ ችግር እየኾኑ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሕግ የበላይነትን በሕገ ወጦች ላይ ለማስተግበር በሚደረገው ጥረት ሕዝቡ ከሰራዊቱ ጎን በመቆም እና የሰላም ኃይል በመሆን አካባቢውን እንዲያስከብርም ጠይቀዋል፡፡

በአማራ ክልል የሕዝቦች ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ የምንችለው ሕዝቡ የራሱን ሰላም ለመቆጣጠር ቆርጦ በመነሳት ከሰራዊታችን ጋር በአንድነት ሲቅም ነው ሲሉም ተናግረዋል።

መከላከያ ሰራዊት በተሰማራበት ሁሉ ወጣቶች በመምከር እና እንዳይደናገሩ በማድረግ ወደ ሰላማዊ ሕይወት እየመለሰ ስለመኾኑም ገልጸዋል። ወጣቶች የአካባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅ የሰላም ሰራዊትነታቸውን እያረጋገጡ ይገኛሉም ብለዋል፡፡

ይህንንም አጠናክረው ሊቀጥሉ ማስገንዘባቸውንም የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የምስራቅ ዕዝ ሚዲያ ወግቧል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየመሬት ግብር ገቢ እስከ 60 በመቶ መጨመሩን የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ገለጸ።
Next articleየደረሱ ሰብሎች ፈጥኖ መሰብሰብ እና የመስኖ ሥራዎችን ማስጀመር የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ እንደኾነ ግብርና ቢሮ ገለጸ፡፡