
ባሕር ዳር: ኅዳር 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የመሬት ይዞታ ማረጋገጥ እና ምዝገባ ተግባራዊ በኾነባቸው አካባቢዎች የመሬት ግብር ገቢ እስከ 60 በመቶ መጨመሩን የክልሉ መሬት ቢሮ ገለጿል። የይዞታ ማረጋገጥ እና ምዝገባ ተግባራዊ መደረጉ የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ከማሳደግ ባለፈ ከመሬት ጋር በተገናኘ ይነሱ የነበሩ ችግሮችን መቀነሱንም ቢሮው ገልጿል።
የአማራ ክልልን የመሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም ከ1989 ዓ.ም ጀምሮ በተለመደው የአሠራር ደረጃ የመሬት መረጃዎችን የመመዝገብ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል። ይሁን እንጅ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ እና የገጠር መሬት መረጃ አሥተዳደር ሥርዓቱን ለማዘመን በአዋጅ 252/2009 የሕግ ሽፋን ተሰጥቶት የሁለተኛ ደረጃ የይዞታ ማረጋገጥ እና ምዝገባ ሥራ (ካዳሥተር) እንዲጀመር መደረጉን የአማራ ክልል መሬት ቢሮ የገጠር መሬት አሥተዳደር እና ካዳስተር ዳይሬክተር ታከለ ሀብቴ ነግረውናል።
የሁለተኛ ደረጃ የይዞታ ማረጋገጥ እና ምዝገባ ሥራ (ካዳሥተር) በዋናነት የካርታ እና ገላጭ መረጃዎችን ያካተተ አሠራር ነው። የካርታ መረጃው የእያንዳንዱ ባለይዞታ ማሳ መገኛ ቦታ፣ ወሰን፣ ስፋት፣ ቅርጽ፣ አጎራባች ይዞታዎች እና አዋሳኝ መንገዶችን የሚያሳይ ነው።
ገላጭ መረጃ ደግሞ የባለይዞታውን ማንነት (ስም፣ አድራሻ፣ ጾታ፣ የጋብቻ ሁኔታ እና ሌሎችንም) በይዞታው ላይ ያለው መብት፣ ክልከላ እና ኀላፊነት፣ የቦታው አገልግሎት እና ደረጃ እንደ ካዳስተር ዓይነቱ ተዘርዝረው የሚያዙ መረጃዎችን ያካትታል፡፡ እነዚህ የመረጃ ዓይነቶች በልዩ የይዞታ መለያ ተገናኝተው ይቀመጣሉ።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት የካዳስተር ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ይገኛል፡፡ እስከ ጥቅምት/2016 ዓ.ም በክልሉ ከሚገኙ ከ4 ሚሊዮን 362 ሺህ በላይ የመሬት ባለይዞታዎች ውስጥ ከ60 በመቶ በላይ የሚኾኑት የሁለተኛ ደረጃ አረንጓዴ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር እንዲያገኝ ተደርጓል፡፡ በክልሉ ካለው ከ18 ነጥብ 1 ሚሊዮን ማሳ ውስጥ ደግሞ ከ62 በመቶ በላይ ማሳ የሁለተኛ ደረጃ ይዞታ ማረጋገጫ ተሠርቶለታል፡፡ ከ148 ወረዳዎች ውስጥ በ117 ወረዳዎች የማረጋገጥ እና የመመዝገብ ሥራ መሠራቱንም ነው ዳይሬክተሩ የገለጹልን።
በተለይም ባለፉት አራት ዓመታት ደግሞ ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እንደተሠራ ነው የገለጹት። የምዝገባ ሥራውን በ2022 ዓ.ም ለማጠናቀቅ በዕቅድ ቢቀመጥም ከተቀመጠው እቅድ ቀድሞ ለማጠናቀቅ ሥራውን የሚያቀልሉ እና ወጭ ቀናሽ አዳዲስ የቴክኖሎጂ አማራጮች ጥቅም ላይ ማዋል ተጀምሯል ብለዋል።
የሁለተኛ ደረጃ የይዞታ ማረጋገጥ እና ምዝገባ ሥራ (ካዳሥተር) የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እና ከመሬት ጋር የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
የካዳስተር ሥራ ሙሉ በሙሉ ተደራሽ በኾነባቸው ወረዳዎች የተዘለሉ ማሳዎች ሁሉ ወደ ግብር ሥርዓት እንዲገቡ ተደርጓል። በዚህም የወረዳዎች የገቢ ግብር እስከ 60 በመቶ መጨመሩን አንስተዋል። ከመሬት ጋር ተያይዞ ይከሰቱ የነበሩ አለመግባባቶች እና ይፈጸሙ የነበሩ ወንጀሎች ቀንሰዋል።
በባሕላዊ መንገድ ይካሄድ የነበረውን የመሬት ልውውጥ (ግብይት) አስቀርቷል። ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትልቅ አቅም ፈጥሯል። አርሶ አደሮች መሬታቸውን ዋስትና በማስያዝ የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ ኾነዋል። መሬቱ በመንግሥት ለልማት ሲፈለግ ደግሞ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንዲኾኑ አስገዳጅ ተደርጎ ይወሰዳል። ጉልበታቸውን ተጠቅመው መሬታቸውን ማልማት ለማይችሉ የኅበረተሰብ ክፍሎች በተመጣጣኝ ዋጋ አከራይተው እንዲጠቀሙ አድርጓል። ይህም በአቅም ማጣት ምክንያት ጾም የሚያድር መሬት እንዳይኖር አድርጓል። በአንድ የእርሻ መሬት በተለያዩ አርሶ አደሮች ይወጣ የነበረውን አረንጓዴ ደብተር አስቀርቷል፡፡ በመሬት ጉዳይ ይጨናነቁ የነበሩ የፍርድ ቤቶች የክርክር ጉዳዮችንም ቀንሷል፡፡ የእርሻ፣ የአትክልት፣ የወል፣ የደን መሬቶችን የአጠቃቀም ሕግም ተግባራዊ በማድረግ እንዲለሙ እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!