
ባሕር ዳር: ኅዳር 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ትናንት በተካሄደው የደቡብ አሜሪካ ዞን የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ ብራዚል ሽንፈት ገጥሟታል።
ሪዮ ዲ ጄኔሮ በሚገኘው እና 78ሺህ 838 ተመልካች በሚይዘው ማራካኛ ስታዲየም ነው በአርጀንቲና አንድ ለ ዜሮ የተረታችው ፡፡ ግቧንም ኒኮላስ ኦታሜንዲ በ63ኛው ደቂቃ አስቆጥሯል፡፡ የአርጀንቲና የበላይነት ወስዳ ማሸነፏን አሶሼትድ ፕሬስ በድረ ገጹ አስነብቧል፡፡
በብራዚል በኩል በ81ኛው ደቂቃ የኒውካስትሉ ጆኢሊንተን በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል፡፡ የብራዚል አሰልጣኝ ፈርናንዶ ዲኒዝ ሽንፈቱን”ሞት ነው” ሲሉ ገልጸውታል፡፡
የአርጀንቲና አሠልጣኝ ሊዮኔል ስካሎኒ “ይህ አስደሳች ድል ነው፤ ብራዚልን ማሸነፍ ቀላል አይደለም ብለዋል። እኛ ግን ማሸነፍ ችለናል» ብለዋል፡፡
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ደጋፊዎች በፈጠሩት ሁከት ምክንያት ዘግይቶ መጀመሩን አሶሼትድ ፕሬስ አስነብቧል ፡፡ሽንፈቱን ተከትሎ የብራዚል ብሄራዊ ቡድን በቀጣይ የዓለም ዋንጫ ላይ የመሳተፏ ነገር ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።ብራዚል በሰባት ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ለይ ትገኛለች።
ሌሊቱን ሌሎች የደቡብ አሜሪካ ሀገራት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎችም ተካሂደዋል። ኮሎምቢያ ፓራጓይን አንድ ለ ዜሮ ስታሸንፍ፣ ኡራጓይ ቦሊቪያን ሦስት ለ ዜሮ ረታለች።
ኢኳዶር ቺሊን ድል ስታደርግ ፔሩ እና ቬኔዝዌላ አንድ አቻ ተለያይተዋል፡፡
አስር ሀገራት እየተሳተፉበት በሚገኘው የደቡብ አሜሪካ ዞን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች አርጀንቲና አስራ አምስት ነጥብ በመሰብሰብ ትመርዋለች። ኡራጓይ በአስራ ሦስት፣ ኮሎምቢያ ደግሞ በአስራ ሁለት ነጥብ ይከተላሉ።
በአሜሪካ፣ ሜክሲኮ እና ካናዳ ጥምረት በሚዘጋጀው የ2026 የዓለም ዋንጫ አርባ ስምንት ሀገራት ይሳተፋሉ። ከደቡብ አሜሪካ ዞን ስድስት ሀገራት በቀጥታ አላፊም ይኾናሉ፡፡ ሰባተኛ ደረጃ ይዞ የሚያጠናቅቀው ሀገር ደግሞ ከሌላ አህጉር ሀገር ጋር የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ያከናውናል።
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!